በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዳያስፖራ አባላት ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኢስተርንኬፕ ግዛት ፖርትኤልሳቤት አካባቢ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋር ተወያይቷል፡፡
በሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች መብትና ጥቅም ማስጠበቅ፣ በዳያስፖራ ልማትና ተሳትፎ እንዲሁም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ነው ኤምባሲው ከዳያስፖራ አባላቱ ጋር የተወያየው።
በውይይቱ በአካባቢው ያሉ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ አደረጃጀት በማቋቋም እያጋጠሟቸው ያሉትን የጋራ ችግሮች ለመቅረፍ ከኤምባሲው፣ ከአካባቢው ማህበረሰብና ከሀገሪቱ የአስተዳደር አካላት ጋር በመቀናጀት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዜጎች የሥራና ደህንነት ሥጋቶችን በሚደቅኑ እና ሀገራዊ ገጽታን በሚያጠለሽ ድርጊቶች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ከድርጊቶቻቸው እንዲቆጠቡ መልዕክት ተላልፏል፡፡
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ መካከል በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን አሳልፎ ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት በቅርቡ የተፈረመ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች በተደራጁ ህገ-ወጥ ቡድኖች አማካኝነት በኢትዮጵያውያን የንግድ መደብሮች ላይ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የተጀመረውን የትብብር እንቅስቃሴ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተነግሯል፡፡
በመጨረሻም የዳያስፖራ አባላቱ በሀገር ቤት በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተሳትፏቸውን በማጠናከር ራሳቸውንና ሀገራቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!