Fana: At a Speed of Life!

የብሔራዊ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂ መጽደቅ ማብሰሪያ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአቅም ችግር ምክንያት የሕግ አገልግሎት ማግኘት የማይችሉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የብሔራዊ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂ መጽደቅ ማብሰሪያ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደውን ጨምሮ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሞድና የፌዴራልና የክልል ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

አቶ ዓለምአንተ አግደው በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ዜጎች የፍትሕ እና የሕግ አገልግሎት የማግኘት መብታቸው በሕገ መንግሥት ላይ የተቀመጠ ቢሆንም በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ አለ።

በአቅም ችግር ምክንያት የሕግ አገልግሎት ማግኘት የማይችሉ ሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ለሌሎች ህብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የሕግ አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ የወጥነት ችግሮች እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።

አሁን የጸደቀው ብሔራዊ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂ መሰል ችግሮችን በመፍታት አቅም የሌላቸው ዜጎች በአግባቡ የሕግ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያግዝ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ማጠናከር ሌላው የስትራቴጂው ዓላማ መሆኑንም ተናግረዋል።

ስትራቴጂው ተግባራዊ ሆኖ የሚጠበቀው ውጤት እንዲመጣ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሰገንዝበዋል።

በፍትህ ሚኒስቴር አዋጅ ቁጥር 1263/2014 እና በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(ሀ) መሰረት አግልግሎቱ ከጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲዉል መወሰኑ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.