Fana: At a Speed of Life!

 የቱሪዝም ሚኒስትሯ በጎንደር ከተማ ህይወት በአብያተ መንግሥት መርሐ ግብርን አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በጎንደር ከተማ ህይወት በአብያተ መንግሥት መርሐ ግብርን አስጀምረዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ሚኒስትሯ እንዳሉት÷ ህይወት በፋሲል አብያተ መንግሥት የጎብኝዎች ቁጥር ከማሳደግ ባለፈ ታሪካዊ ሁነቶችን ለማወቅ ይረዳል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ  የተከናወነው የጎንደር ፋሲል አብያተ መንግሥት ዕድሳት ስራ በስኬት መከናወኑን አስታውሰው፤ ይህም የፋሲል አብያተ መንግሥት ይበልጥ እንዲጎበኝ እና የቀደሙ የነገሥታቱን ክዋኔዎች በትውልዱ እንዲዘከሩ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

ከቅርሱ ጥገና ባለፈ ህይወትን በቅርሱ ለመዝራት መንግሥት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በጎንደር አብያተ መንግሥት የጀመረው ህይወት በአብያተ መንግሥት መርሐ ግብር በቀደመው ጊዜ ነገሥታቱ ይከውኗቸው የነበሩ ሁነቶችን ከመመለስ ባለፈ ጎብኝዎች የታሪኩ አካል እንዲሆኑ ለማድረግ ታሰቦ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡

ይህ እሳቤ የጎብኝዎችን ቆይታ ጊዜ እንደሚያራዝም ገልጸው÷ መርሐ ግብሩ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ባሉ አብያተ መንግሥታት እንዲሰፋ ይደረጋል ነው ያሉት።

መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ የብዝሃ ድንቅ የቱሪዝም ሀብት ባለቤት መሆኗን በግልፅ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ በበኩላቸው÷ ትውልዱ የቀደሞ አባቶችን ገድልና ስራ በሚገባ ማወቅ እንዲችል ዕድል መፍጠር እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በፋሲል አብያተ መንግሥት ግብረ ህንፃ ግቢ ውስጥ ነገስታቱ ህይወታቸውን እንዴት መኖር እንደቻሉና የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶችና የታሪክ አካል የሆኑ ክዋኔዎችን ማሳየት መጀመሩ ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

ክልሉ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዳሉት ጠቅሰው÷ በመዳረሻዎቹ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በዛሬው መርሐ ግብር ነገሥታቱ ሲከውኗቸው የነበሩ ተግባራት የሚያሳዩ የጥንት ክዋኔዎች ላይ 300 የተለያዩ የሙያ ባለቤት የሆኑ ሰዎች ተሳትፈዋል።

በምናለ አየነው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.