ቦምብ ይዞ ሲንቀሳቀስ በጉሙሩክ ተቆጣጣሪዎች የተያዘው ተከሳሽ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለት ቦምቦችን ይዞ ሲንቀሳቀስ በጉሙሩክ ኬላ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች በፍተሻ ተይዟል የተባለው ተከሳሽ በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወሰነ።
ውሳኔውን ያሳለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በተከሳሹ እጅ ላይ ተይዘው በኢግዚቢት የተቀመጡ ቦምቦች ለመንግስት ገቢ እንዲሆኑ ወስኗል።
የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያመላክተው እንየው ጣፈጠ የተባለው ተከሳሽ ፍቃድ ሳይኖረው በየካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ከረፋዱ 4:00 ሰዓት ላይ መነሻውን ጦላይ በማድረግ ወልቂጤ ከተማ አበሽጌ ወረዳ የጉሙሩክ የፍተሻ ጣቢያ ሲደርስ በተደረገበት ፍተሻ አንድ የእጅ ቦምብ እና ሌላ አንድ የጭስ ቦምብ ደብቆ ይዞ ተገኝቷል።
በዚህም የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 22 ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፏል በሚል ክስ አቅርቦበታል።
ተከሳሹ በተፈቀደለት የዋስትና መብት ከእስር ውጭ ቢሆንም የህግ ግዴታውን ግን አክብሮ በሌሎች የችሎት ቀጠሮዎች ሳይቀርብ ቀርቷል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሹ የወጀል ተግባሩን መፈጸሙ መረጋገጡን ገልጾ፤ በተከሰሰበት ድንጋጌ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፎበታል።
ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ አለማቅረቡን ተከትሎ ተከሳሹ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ አለመኖሩ በቅጣት ማቅለያነት በመያዝ በዕርከን 24 መሰረት በ6 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራትና በሁለት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።
ፖሊስ ተከሳሹን አፈላልጎ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ታዟል።
በታሪክ አዱኛ