Fana: At a Speed of Life!

ከ1 ሺህ 800 ካሬ ሜትር ይዞታ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል የተከሰሱት የቀድሞ የመዲናዋ ከንቲባ አማካሪን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ማረሚያ እንዲወርዱ ታዘዘ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ሺህ 800 ካሬ ሜትር ይዞታን በተለያዩ መጠን ያለአግባብ ግለሰቦች እንዲወስዱ በማድረግና በየደረጃው ይዞታውን ተቀብሎ በመሸጥ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ተብለው በሙስና ወንጀል የተከሰሱት የቀድሞ የመዲናዋ ከንቲባ አማካሪን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ታዘዘ።

ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና የወንጀል ችሎት ነው።

ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የታዘዙ ተከሳሾች የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽ/ቤት የካሳ ግምትና ምትክ ባለሙያ አፈወርቅ ሀይሌ፣ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አማካሪ ቶሎሳ ተስፋዬና የቀድሞ የአ/አ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ የሰው ኃይል ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አበበ ደጋ ይገኙበታል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ11 የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞችና 13 ግለሰቦች በአጠቃላይ በ24 ተጠርጣሪዎች ላይ ባለፈው አርብ የተጠርጣሪዎችን የወንጀል የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነትና በልዩ የሙስና ወንጀል ተካፋይነት በመሆን የስልጣን አላግባብ መገልገል የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ አቅርቧል።

ክሱ ለተከሳሾቹ ከደረሰ በኋላ ዛሬ በንባብ ተሰምቷል።

ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ)፣ ንዑስ ቁጥር 3 እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና (ለ) እንዲሁም ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተጠቀሰውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚል ክስ ነው የቀረበባቸው።

በዚህ በቀረበባቸው ክስ ላይ ከ1ኛ እስከ 9ኛ እንዲሁም 23ኛ እና 24ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሱት ተከሳሾች የመንግስት የስራ ሃላፊነት ላይ ተመድበው ሲሰሩ በልዩ ወንጀል አድራጊነት የሙስና ወንጀል ተካፋይ ከሆኑት ከ10ኛ እስከ 22ኛ ከተጠቀሱት በግል ስራ ከሚተዳደሩት ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ ሕዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት የተለያዩ ቀናት ውስጥ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ወረዳ 01 እና በልደታ ወረዳ 3 በይዞታ ክልል ውስጥ በአርሶ አደርና በአርሶ አደር ልጆች በሚል ምክንያት ብቻ ተገቢ ያልሆነ የካሳና ምትክ እንዲወስዱ መደረጉ በክሱ መገለጹ በንባብ ተሰምቷል።

በአጠቃላይ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት ተከሳሾቹ በተለያዩ መጠኖች 1 ሺህ 800 ካሬ ሜትር ይዞታን በህገ ወጥ መንገድ የተጠቀሱት ግለሰቦች እንዲወሰዱ በማድረግ እና ሌሎቹ ተከሳሾች ወስዶ በመሸጥ ለራሳቸዉ የማይገባቸዉን ብልፅግና በማግኘት እንዲሁም በመንግስት ላይም የመሬቱ ሊዝ ዋጋ የሆነዉን እና ካሳ የተከፈለዉን 80 ሚሊየን 755 ሺህ 508 ብር ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ የሙስና ወንጀል ተካፋይነት በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ መቅረቡ በንባብ ተሰምቷል።

ተከሳሾቹ ካሉበት ጊዜያዊ የፖሊስ ማቆያ ችሎት ቀርበው የቀረበባቸው ክስ በችሎት አዳምጠዋል።

ፍርድ ቤቱም ተከሳሾቹ ካሉበት ጊዜያዊ የፖሊስ ማቆያ ወደ ማረሚያ ወርደው በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በማዘዝ ለታህሳስ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.