ኢትዮጵያ ለፍልሰተኞች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የገባችውን ቃል ኪዳን ተግባራዊ ታደርጋለች – አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 5 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ፍልሰተኞችን ለመደገፍ እና ምላሽ ለመስጠት የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የድጋፍ ማዕቀፍ እየተገበረ እንደሚገኝ ተገለጸ።
በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተካሄደው ዓለም አቀፍ የፍልተኞች የምክክር መድረክ ጎን ለጎን በኢጋድ የድጋፍ ማዕቀፍ ላይ የመከረ ስብሰባ ተካሂዷል።
በስብሰባው ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፥ ኢትዮጵያ ፍልሰተኞችን ለመደገፍ የቀረፀችውን ስድስት አዳዲስ ቃል ኪዳኖች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
አቶ ደመቀ በቀጠናው ለሚገኙ ፍልሰተኞች ኢጋድ እያደረገ ለሚገኘው ሰብአዊ ድጋፍ እና እያከናወነ ላለው የዘላቂ ልማት ስራዎች ምስጋና አቅርበዋል።
የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው የፍልሰተኞችን ህይወት ለመደገፍ የተገቡ ቃል ኪዳኖች በውጤታማነት ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ የሚደረጉ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፎች መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
በተጨማሪም የስደተኞች እና ተመላሾች ጉዳይ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን ኢትዮጵያ ለፍልሰተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አስፈላጊ ሰነዶችን በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ እድገት አሳይታለች ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።