Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል አዛዦች የኢትዮጵያ አየር ኃይል አቅምን የተመለከቱበት ጉብኝት ማድረጋቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል አዛዦች በኢትዮጵያ አየር ኃይል ያደረጉት ጉብኝት ተቋሙ እየገነባ ያለውን አቅም ለመረዳትና ልምድ ለመቅሰም እንዳስቻላቸው ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “በመሥዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል” በሚል መሪ ሃሳብ ከሕዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።

የመርሐ-ግብሩ አንድ አካል የሆነው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም በቢሾፍቱ መካሄዱ የሚታወቅ ሲሆን፥ በፎረሙ የተሳተፉ የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች የኢትዮጵያ አየር ኃይልን የለውጥ ሥራዎች ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የተሳተፉት የቦትስዋና አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሀንድሪክ ራካንዝዋና፥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተሟላ አቅም እንዳለው መመልከት መቻላቸውን ገልፀዋል።

ቦትስዋና የአየር ኃይል አብራሪዎቿን በኢትዮጵያ ማሰልጠንን ጨምሮ በዘርፉ ያላትን አቅም ለማሳደግ ከኢትዮጵያ ትምህርት መውሰድ እንደምትፈልግም ነው የተናገሩት።

የአፍሪካ አየር ኃይሎችን የጋራ አቅም ለማስተባበር የተጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑንም አመልክተው፤ በትብብር በመሥራት ያሉብንን ችግሮችና ፈተናዎች በጋራ የመፍታት አቅማችንን ይበልጥ ማጎልበት ይገባናል ሲሉም ነው የገለጹት።

የዩጋንዳ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ቻርለስ ኦኪዲ በበኩላቸው፥ በጉብኝቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያለውን የመፈጸም አቅም ማየት ማየት ችለናል ብለዋል።

ዩጋንዳ ከኢትዮጵያ ጋር በአየር ኃይል ዘርፍ ያላትን ትብብር ማሳደግ እንደምትሻም ጠቁመዋል።

አፍሪካ በማደግ ላይ የምትገኝ አህጉር መሆኗንና ዓለም በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደምትገኝ ጠቅሰው፥ ወታደራዊ ትብብርን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነም አንስተዋል።

አፍሪካውያን የራሳቸውን አቅም በዘላቂነት መገንባት እንዳለባቸውም ሌተናል ጄኔራሉ ገልጸዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.