በኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ ከተመድ ምክትል ዋና ፀሃፊ ጋር ተወያዬ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር የተመራ ልዑክ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ምክትል ዋና ፀሃፊ አሚና መሐመድ ጋር ወላጆቻቸውን ያጡና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዬ፡፡
በሚኒስትሯ የተመራው ልዑክ ከተመድ የተለያዩ ኤጀንሲዎች ጋርም እየመከረ ነው ተብሏል፡፡
ልዑኩ ከድርጅቱ ምክትል ዋና ፀሃፊና በኒውዮርክ የዘላቂ ልማት ቡድን ሊቀመንበር አሚና መሐመድ ጋር ባደረገው ውይይት በኢትዮጵያ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል።
በማህበረሰቡ ውስጥ ላሉ ችግሮች ኢትዮጵያውያን መፍትሄ አቅራቢዎች እንዲሆኑ ማድረግ ላይ ያተኮረ ውይይት መሆኑንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ ኢትዮጵያ እነዚህን ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የጀመረችውን ፕሮግራም ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ ተጨባጭ የሆነ የማህበረሰብ ለውጥ ለማምጣት ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።
በውይይቱ መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር ያደረገው አሊያንስ ናው የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት ተሳትፏል ተብሏል፡፡