Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋምና የምግብ ዋስናን የማረጋገጥ ስራዎች ለሀገራት አብነት እየሆኑ መምጣታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በረሃማነትን ለመከላከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስናን ለማረጋገጥ የምታከናውናቸው ስራዎች ለበርካታ ሀገራት አብነት እየሆኑ መምጣታቸውን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በኳታር ዶሃ እየተካሄደ በሚገኘው የ2023 ኢንተርናሽናል የአትክልት እና ፍራፍሬ ኤክስፖ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያን ግብርና ምርቶች የሚያስተዋውቀው “ፓቪሊዮን” የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታዋ ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር) በተገኙበት ተከፍቷል፡፡

በመክፈቻ ፕሮግራሙ በኳታር የኤክስፖ 2023 ዶሃ ኮሚሽነር ጀነራል አምባሳደር ባድር ቢን ኦመር አል ዳፋ፣ የኤፌዲሪ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች ታድመዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታዋ ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ስርዓት በመዘርጋት ለዘላቂና ሁሉን አቀፍ ዕድገት አዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጥቶ ወደ ተግባር ተሸጋግሯል፡፡

በዚህም ሀገሪቱ የዜጎቿን ፍላጎት ለመመለስና የበለፀገ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል የ10 አመት እቅድ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥንና የአካባቢ መራቆትን ለመቋቋም የወጠነችውን ትልም ለማሳካት ሀገር በቀል ስልቶችን መከተሏን በመግለጽ ስራዎቹም ለሀገራት አብነት እየሆኑ መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡

እንዲሁም በረሃማነትን ለመከላከል በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመሥራትም የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወኗን እንደገለጹ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.