የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የልማት ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የልማት ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የህብረቱ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ገለጹ፡፡
አምባሳደር ሮላንድ÷የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር በልማት እና ሌሎች ዘርፎች ጠንካራ ትብብር እንዳለው አንስተዋል።
ከሳምንት በፊት የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት አምባሳደሮች ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ያደረጉት ውይይት ውጤታማ እንደነበርም አስታውሰዋል።
በዚሁ ጊዜ በፖለቲካ፣ ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት፣ ሰብአዊ መብት፣ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ህብረቱ ድጋፍ በሚያደርግባቸው ሌሎች ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ህብረቱ ድጋፍ ማድረግ በሚችልባው ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመምከር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በማስፈን የተረጋጋ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት እያከናወነች ላለው ተግባር ህብረቱ ድጋፉን እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሀገሪቱ የሚታዩ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ጠንካራ አገረ መንግስት ለመገንባት እየተሰራበት የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።
በቀጣዩ የፈረንጆች አዲስ ዓመት ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በትምህርት፣ ጤና፣ ማህበራዊ ዘርፎች፣ መሰረተ ልማት ላይ በትብበር መስራቱን እንደሚቀጥል አምባሳደሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የውስጥ መሰረተ ልማቷን በማስፋፋት እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የልማት ትስስር በመፍጠር የእርስ በርስ ግንኙነትና ምጣኔ ሃብትን ለማቀላጠፍ እያከናወነች ያለውን ተግባር እንደግፋለን ብለዋለ።
የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር በልማት፣ በምጣኔ ሃብትና ሌሎች ዘርፎች ያለውን ትብብሩን እንደሚቀጥል አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።