Fana: At a Speed of Life!

አቶ አረጋ ከበደ መንግሥት ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በየደረጃው የሥራ አጥነት መንሰራፋት አሁን ላይ ለተፈጠረው የጸጥታ ችግር አንዱ መንስኤ መሆኑን በማመን መንግሥት ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ አስታወቁ፡፡

በባሕር ዳር ከተማ የሥራ ላይ ልምምድ ሲያደርጉ የነበሩ ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶች ተመርቀዋል።

ዛሬ የተመረቁት ወጣቶች በከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ታቅፈው በመሰልጠን የሥራ ላይ ልምምድ ሲያደርጉ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል።

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በምረቃ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በከተማ የምግብ ዋስትና የታቀፉ ሥራ አጥ ወጣቶችን በማሰልጠን፣ የሥራ ላይ ልምምድ በመስጠትና በመቅጠር ባለሃብቶችና የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

እንደ ክልል አሁን ላይ ከሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው ሥራ አጥነት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በየደረጃው የሥራ አጥነት መንሰራፋት አሁን ላይ ለተፈጠረው የጸጥታ ችግር አንዱ መንስኤ መሆኑን በማመን መንግሥት ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ዴዔታ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው÷ በአሁኑ ወቅት ባሕር ዳርን ጨምሮ በ11 ከተሞች ሥራ አጥ ወጣቶችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በማሰልጠን በግልና በመንግሥት ድርጅቶች እንዲቀጠሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተሞች የምግብ ዋስትና እያስገኘ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በአግባቡ በመጠቀም ወጣቶች የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት መቀየር እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.