የሰላም ጀግኖች ሆነን ሕዝባችንን እንክሳለን – የተሃድሶ ሠልጣኞች
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በሸዋ ኮማንድ ፖስት ለ10 ቀናት ለ3ኛ ዙር የተሃድሶ ሥልጠና ሲከታተሉ የቆዩ 161 ስልጠናቸውን አጠናቀዋል።
የተሃደሶ ሥልጠናውን የተከታተሉት በሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አሥተዳደር እና የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ታራሚዎቹ ሲሆኑ፤ በክልሉ ተከስቶ በነበረው ግጭት፣ ሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ሥር የቆዩ ናቸው።
ሠልጣኞቹ በማዕከሉ ቆይታቸው በተለያዩ ርዕሶች ላይ የተዘጋጀውን ሥልጠና መውሰዳቸው የተገለፀ ሲሆን÷ ከ161 ተመራቂዎች መካከል አምስቱ ሴቶች ናቸው መባሉን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ተመራቂዎቹ በማረሚያ ቤቱ ቆይታ ያሳዩት ሥነ ምግባር ጨዋነት የተሞላበት እንደነበር ተገልጾ ወደ ኅብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ለአካቢያቸው ሰላም በኀላፊነት እንዲሠሩ መልእክት ተላልፏል።
ሠልጣኞቹ÷ በማኅበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ በመታለል በስሜታዊነት ወደ አመጽ መግባታቸውን ተናግረው፤ ወደ ስህተት የሚመራንን የሀሰት ወሬ አንሰማም፤ የሰላም ጀግኖች ኾነን ሕዝባችንን እንክሳለን ሲሉ ገልፀዋል።
ከኅብረተሰቡ ጋር በሚቀላቀሉበት ወቅት ሌሎች ወጣቶች እንዳይታለሉ ለማስተማር ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።