ፓስፖርትና ቪዛ ለውጭ ዜጎች በመስጠትና ግለሰቦችን ወደ ውጭ በመላክ የሙስና ወንጀል ለተከሰሱ 38 ሰዎች የክስ ዝርዝር ደረሰ
አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 8 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፓስፖርትና ቪዛ ለውጭ ሀገር ዜጎች በመስጠትና ሰነድ አልባ ግለሰቦችን ወደ ውጭ በመላክና በተያያዥ የሙስና ወንጀል ለተከሰሱ 38 ተከሳሾች የክስ ዝርዝር እንዲደርስ ተደረገ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዘርፍ ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ረቡዕ የተከሳሾቹን የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ በ60 ግለሰቦች ላይ በየደረጃው 15 የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
በአጠቃላይ 60 ሺህ ገጽ የሰነድ ማስረጃዎችና የክስ ዝርዝሩ በፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር በኩል ተመሳክሮ ባለመጠናቀቁ ምክንያት ክስ ዝርዝሩንና የሰነድ ማስረጃውን ለመጠባበቅ ለዛሬ በተሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የደረሰውን የክስ ዝርዝርና የሰነድ ማስረጃዎችን ለቀረቡ ለ38 ተከሳሾች እንዲደርስ አድርጓል።
ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ከተደረጉ 38 ተከሳሾች መካከል በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የምዝገባና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምሩ ግንበቶ አዋልሶ፣ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የውጪ ዜጎች ቁጥጥርና ቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር፣ጅላሉ በድሩ ሰማ፣ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቡድን አስተባባሪ ከድር ሰዒድ ስሩር፣ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የኬላዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ቦጋለ በዳዳ ይገኙበታል።
ሌሎች 22 ተከሳሾች ግን ችሎት ያልቀረቡ ሲሆን ችሎት ካልቀረቡት መካከል ሁለቱ ቀደም ብሎ በምርመራ ላይ እያሉ በዋስ መፈታታቸውን ዐቃቤ ሕግ ለችሎቱ ገልጿል።
ሌላ ችሎት ያልቀረበ አንድ ተከሳሽን በሚመለከት ደግሞ ከአሶሳ ከተማ በቁጥጥር ስር ውሎ ዛሬ በአውሮፕላን እየመጣ መሆኑን አብራርቷል።
ፍርድ ቤቱ ክስ እንዲደርሳቸው የተደረጉ 38 ተከሳሾችን ማንነት የማረጋገጥ ስራ አከናውኗል።
በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ 54ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰ ፈራኦል የተባለ ተከሳሽ ላይ ያቀረበው ክስ እንዲቋረጥለት ለችሎቱ አመልክቷል።
የፍርድ ቤቱም በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ መሰረት ክሱ እንዲቋረጥ አድርጓል።
በዚህ በተመሰረተባቸው ክስ ላይ የተመላከተባቸው ድንጋጌ ዋስትና መብት የማያስከለክል መሆኑን ተከትሎ የኢሚግሬሽን ዜግነት አገልግሎት የኬላዎች ዘርፍ ቡድን መሪ የነበረው 5ኛ ተከሳሽ አይክፋው ጓሳዬ ገረመው እና አለሚቱ የኔ አየሁ የተባለች 49ኛ ተከሳሽን በሚመመከት በጠበቆች በኩል የዋስትና መብት ይፈቀድልን የሚል ጥያቄ ተነስቷል።
በዐቃቤ ሕግ በኩል ዋስትና ጥያቄ ላይ መቃወሚያ ያልቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱ 5ኛ ተከሳሽን በ20 ሺህ እና 49ኛ ተከሳሽን ደግሞ በ10 ሺህ ብር ዋስ አሲዘው ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የችሎቱ ዳኞች በአጠቃላይ የቀረበው ክስ ዝርዝር ዛሬ እንደደረሳቸው በመጥቀስ ክሱን ተመልከቶ በችሎት በንባብ ለማሰማት ለታህሳስ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ያልቀረቡ ተከሳሾችን የፌደራል ፖሊስ በአድራሻቸው አፈላልጎ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ አዟል።
በሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር ከህግ ውጪ ጉቦ በዶላር እየተቀበሉ ለውጭ ዜጎች ከህግና አሰራር ውጪ ቪዛ በመስጠት፣ ሰነድ አልባ ዜጎችን በህገወጥ መንገድ ከሀገር በማስወጣት፣ መንግስት ላይ ጉዳት ማድረስ የሚሉ ነጥቦች በየተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ በክስ ዝርዝሩ ተካቷል።
በታሪክ አዱኛ