በመዲናዋ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለማስወገድ የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች በአዲስ አበባ ከተማ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ በአዲስ አበባ በተካሄደ ኦፕሬሽን የእገታ ወንጀል፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያና የተደራጀ ከባድ የዝርፊያ ወንጀል ፈፅመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም ሞተር ሳይክል፣ ባጃጅና የራይድ ታክሲዎችን ተጠቅመው የሰው ግድያ፣ የሞባይል ንጥቂያና ሌሎች ወንጀሎች ፈፅመዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
በርካታ የሺሻ ማስጨሻ፣ የጭፈራና የቁማር ቤቶች እንዲሁም ሕገ-ወጥ የንግድ ሱቆች ላይ በተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ እንዲዘጉ መደረጋቸው ተጠቁሟል፡፡
እነዚህ ወንጀሎች ለኅብረተሰቡ የፀጥታ ሥጋት በማይሆኑበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ተከታታይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ አንደሚቀጥልም ተጠቅሷል፡፡
በየጊዜው ውጤቱ እየተገመገመ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ መገለጹንም የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
የራይድ ታክሲ፣ የሞተር ሳይክልና የባጃጅ አጠቃቀም ሥርዓት እንዲይዝ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሠራና በወንጀል ተሳትፈው ከተገኙ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተጠቁሟል።
በቀጣይ ለሚካሄደው ኦፕሬሽን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ለፖሊስ መረጃ በመስጠት የተለመደ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ ቀርቧል፡፡