ከምትሰራበት መኖሪያ ቤት ህጻን ልጅ ይዛ በመጥፋት የተከሰሰችው ግለሰብ በሰባት ክሶች እንድትከላከል ተበየነ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤት ሰራተኛነት ከምትሰራበት መኖሪያ ቤት የሁለት አመት ህጻን ልጅ ይዛ በመጥፋት (በመጥለፍ) በሱሉልታ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋለችው ተከሳሽ ግለሰብ በሰባት ክሶች እንድትከላከል ብይን ተሰጠ።
የቀረበባትን ማስረጃ መርምሮ ተከሳሿ በቀረቡባት ተደራራቢ ሰባት ክሶች እንድትከላከል ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ነው።
ችሎቱ ከተከሳሿ ጋር አብሮ የተከሰሰ ማለትም በ1ኛ ተከሳሽ የተሰረቀ ላፕቶፕ ኮምፒዩተርን በመግዛት በመሸሸግ ወንጀል የተከሰሰ ግለሰብም በተከሰሰበት ድንጋጌ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል።
የፍትህ ሚኒስቴር የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው ቤዛዊት በቀለ የተባለችው ተከሳሽ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረአበሮቿ ጋር በመሆን በመጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ሳሪስ አዲስ ሰፈር ኤልቤቴል በሚባል አካባቢ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ከምትሰራበት ቤት ሶሊያና ዳንኤል የተባለች የሁለት አመት ህጻንን ጠልፋ (ሰርቃ) ወደ ኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ከተማ መውሰዷ በክሱ ተመላክቷል።
ከዚህም በኋላ የአ/አ ፖሊስ እና የፌደራል ፖሊስ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ባደረጉት ክትትል በሱሉልታ ከተማ ለዚሁ ወንጀል መጠቀሚያ በተዘጋጀ ባዶ ቤት ውስጥ ህጻኗን ይዛ ሳለ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር መዋሏን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል።
በዚህም መሰረት የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና አንቀጽ 590 ንዑስ ቁጥር 1 ለ እንዲሁም ንዑስ ቁጥር 2 (ሠ) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፋለች ተብላ በዋና ወንጀል አድራጊነት ለአካለ መጠን ያልደረሰች ህጻንን መጥለፍ ወንጀል ተከሳ ነበር።
በሁለተኛው ክስ ላይ ደግሞ ይህችው ተከሳሽ ከዚሁ መኖሪያ ቤት የተለያዩ 3 ሞባይል ስልኮችንና 2 ግራም ሀብል ወርቅን ጨምሮ በአጠቃላይ 32 ሺህ 100 ብር የሚገመቱ ንብረቶችን ሰርቃ መሰወሯን በመጥቀስ ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ህግ አንቀጽ 669 ንዑስ ቁጥር 2 (መ) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፋለች በማለት በከባድ የስርቆት ወንጀል ክስ አቅርቦባታል።
በተጨማሪም ተከሳሿ ህጻን ሰርቃ በቁጥጥር ስር መዋሏ በመገናኛ ብዙኃን መረጃው ከተሰራጨ በኋላ ደግሞ በተለያዩ ስሞችን በመጠቀም በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ስትሰራበት ከነበሩ የተለያዩ መኖሪያ ቤቶች ላፖቶፕ ኮምፒዩተርን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶች ተሰርቆብናል ያሉ ግለሰቦች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መሰረት ማጣሪያ ተደርጎ ማስረጃ ከተሰበሰበ በኋላ በተመሳሳይ አምስት ከባድ የስርቆት ወንጀል ክስ ተመስርቶባት ነበር።
ክሱ በችሎት በንባብ ከተሰማና የተከሳሽ የዕምነት ክህደት ቃል ከመዘገበ በኋላ ተከሳሿ በቀረበባት ተደራራቢ ሰባት ክሶች ላይ ዐቃቤ ሕግ የተቆጠሩ 30 ምስክሮችንና 2 በኢግዚቢት የተያዙ ማስረጃዎች እንዲሁም 8 ገላጭ ተንቀሳቃሽና የፎቶ ማስረጃዎች ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም የሰውና የሰነድ ማስረጃዎቹን መርምሮ ተከሳሿ በተከሰሰችበት ተደራራቢ የክስ ድንጋጌዎች ላይ የተጠቀሱ የወንጀል ድርጊቶች መፈጸማቸው መረጋገጡን ጠቅሶ እንድትከላከል ብይን ተሰቷል።
ይህችው አንደኛ ተከሳሽ ከሌላ የግል ተበዳይ ሰርቃለች የተባለውን ግምቱ 53 ሺህ ብር የሆነ ላፕቶፕ ኮምፒዩተርን የተሰረቀ ንብረት መሆኑን እያወቀ በ16 ሺህ ብር ከ1ኛ ተከሳሽ በመግዛት፣ በመሸሸግ ወንጀል የተከሰሰው ሀ/ኢየሱስ ኮርጃ የተባለው ሁለተኛ ተከሳሽን በሚመለከት የቀረበበት ማስረጃን መርምሮ ፍርድ ቤቱ በተከሰሰበት በአንቀጽ 669 ንዑስ ቁጥር 2 ድንጋጌ መሰረት እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።
ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ