አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ከስፔን ጋር ያላትን ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ ደረጃ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ገለፁ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከስፔን ጋር ያላትን ታሪካዊና ሰፊ ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ ደረጃ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የስራ ቆይታቸውን ያጠናቀቁትን የስፔን አምባሳደር ማኑኤል ሳላዛርን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ሽኝት አድርገውላቸዋል።
አቶ ደመቀ በዚሁ ወቅት÷ ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ጊዜያት በገጠሟት ወቅቶች ስፔን ላሰየችው በመርህ ላይ የተመሰረተ እና ወጥነት ያለው አቋም ኢትዮጵያ እውቅና ትሰጣለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከስፔን ጋር ያላትን ታሪካዊና ሰፊ ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ ደረጃ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላትም ገልጸዋል።
አምባሳደር ማኑኤል ሳላዛር በስራ ቆይታቸው የሁለቱን እህትማማች ሀገራት ግንኙነት በማስፋት ረገድ ላደረጉት አስተዋፅኦም አመስግነዋል፡፡
አምባሳደር ማኑኤል በበኩላቸው÷ ስፔን ኢትዮጵያን እንደ ትልቅ አጋር ትቆጥራለች ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በልማት ትብብር፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በአቪዬሽንና በሌሎችም መስኮች ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጨምሯልም ሲሉ አምባሳደሩ ጠቅሰዋል፡፡