የ5 ነጥብ 13 ቢሊየን ብር ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ውል ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከደቡብ ኮሪያ ሃንሶል ፔፐር ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ጋር በ5 ነጥብ 13 ቢሊየን ብር የአደዓ በቾ የከርሰ ምድር ውሃ መስኖ ልማትና የገጠር ልማት ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ውል ተፈራርሟል፡፡
ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች አደዓና በቾ ሜዳዎች አካባቢ የሚከናወን መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
የስምምነት ውሉን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) እና የደቡብ ኮሪያ ሃንሶል ፔፐር ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ዲቭዥን መሪ ዳቪድ ቶሻን ኪም ተፈራርመዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ የክርሰ ምድር ውሃ መስኖ ልማት፣ የመስኖ ልማት ፋሲሊቲ ተከላ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፣ የግብርና ማሰልጠኛ ማዕከልና ተያያዥ ፋሲሊቲዎች እና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ሥራዎችን እንደሚካትት የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም ፕላንት ፓይለት እስማርት የውሃ ማናጅመንት ሲስተም ፣ የግብርና ማሽነሪዎችና ተሸከሪካሪዎች አቅርቦት፣ የህብረተሰብ ድጋፍ ፣ የሙከራ ኦፕሬሽን ለግብርና ማሰልጠኛ ማዕከላትና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፕላንት እንደሚያካትት ተጠቁሟል፡፡