Fana: At a Speed of Life!

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች መስራት ይኖርብናል – የጅቡቲ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ይበልጥ እንዲጠናከር መስራት እንደሚገባ የጅቡቲ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ድልኤታ መሐመድ ድልኤታ ገለጹ፡፡

በዛሬው እለት 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ የምክር ቤት አባላትና ሌሎች የሥራ ሀላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።

የጅቡቲ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ድልኤታ መሐመድ ድልኤታ በምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸውም÷ የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ወዳጅነት ከአመታት በፊት እንደጀመረ በማስታወስ በኢትዮጵያ የጅቡቲ አምባሳደር ሆነው ማገልገላቸውን ጠቅሰዋል።

ሁለቱን ሀገራት በማቀራረብ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ለማስተሳሰር ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ጠቅሰው÷ የሀገራቱ ወዳጅነት እውነተኛ እና ልባዊም ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካ ልዩ እና ተምሳሌት ናችሁ ያሉት ድልኤታ መሐመድ ድልኤታ÷ይሄንንም ዛሬ ከእናንተ ፊት ተገኝቼ ምስክርነት በመስጠቴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት፣ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ባለስጣንን (ኢጋድ) በማጠናከር እንዲሁም በኢኮኖሚዋና በህዝብ ብዛቷ በተለይም ደግሞ በዲፕሎማሲ በባህል እና በስነ-ጽሁፍ ከፍተኛ ቦታ ያላት ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

በጉብኝታቸውም የሀገራቱ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የቱሪዝም እና ስፖርት ግንኙነት እንዲጠናከሩ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ሀገራቱ በትብብር እንዲሰሩ በማድረግ በተለይ ደግሞ ህዝቦች የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ በማስቻልና ወጣቶችም በሀገራቱ በነጻነት እንዲዘዋወሩ በማድረግ መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በዚህም የሁለቱን ሀገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያንና ጅቡቲን ግንኙነት በማጠናከር የሀገራቱ መሪዎች የጀመሯቸውን ስራዎችን ለማጠናከር መተባበር ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ በፊት የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች እንዳሉ ጠቅሰው÷ከእነዚህም መካከል የኤሌክትሪክ ሃይል ትስስር፣ የውሃ ቧንቧና የባቡር ሀዲድ ዝርጋታዎች እንዲሁም የፋይበር ኦፕቲክ ዝርጋታዎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

ለተከናወኑ ስራዎች እውቅና መስጠት እንደሚያስፈልግ እና ግንኙነቱ ለአፍሪካም ምሳሌ እንደሚሆን አውስተዋል፡፡

ጉብኝታቸውም ትብብር እና እርዳታን ለማጠናከር እንዲሁም የተሻሉ ምዕራፎችን ለመክፈት ያለመ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የሀገራቱ ህዝቦች እሴት፣ ለሰላም እና ለብልጽግናም ያላቸው ፍላጎት እንዲሁም የተጋፈጧቸው ችግሮች ተመሳሳይ መሆናቸውን ጠቁመው÷“ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የሚጋፈጧቸው ችግሮች ተመሳሳይ ናቸው” ብለዋል፡፡

በተለይም የወጣቶች ሥራ አጥነት ለሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን ነው የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የገለጹት፡፡

የሚያጋጥሙ ችግሮችን መጋፈጥና ማስወገድ እንደሚገባ፤ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ አንዳቸው ለአንዳቸው የንግድ አጋሮች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የሀገራቱ ትስስር ሌሎች ሀገራትንም ማካተት እንዳለበት በመጥቀስ÷ ሀገራቱ በትብብር ተሳስረው ወደፊት መራመድ እንደሚችሉም አመላክተዋል፡፡

በቀጣይም “ችግሮቻችንን አብረን ሆነን በመጋፈጥ ለልጆቻችን የተሻለ ሰላም እና ብልጽግና ያለበትን ዓለም ማስረከብ እንችላለን” ብለዋል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.