ወላይታ ሶዶ ለከተሞች ፎረም ዝግጅት እያደረገች መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወላይታ ሶዶ ከተማ ከየካቲት 9 እስከ የካቲት 15 ቀን 2016ዓ.ም ለሚከበረው የከተሞች ፎረም ዝግጅት እያደረገች መሆኑ ተገለፀ፡፡
ከተማዋ ከየካቲት 9 እስከ የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከበረውን የከተሞች ሣምንት እንድታዘጋጅ መመረጧ ይታወቃል፡፡
የወላይታ ዞን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፍ አቶ ዘዉዱ ሳሙኤል÷ በከተሞች ፎረም መርሐ ግብር ከ150 በላይ ከተሞች፣ ከ20 በላይ ድርጅቶች እንዲሁም ከ20ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ብለዋል።
ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና የ150 ከተሞች ከንቲባዎችም በዝግጅቱ ይታደማሉ ነው ያሉት።
በዚህም ከክልል ጀምሮ እስከዞን ድረስ የተዋቀረ ኮሚቴ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ለዝግጅቱም 25 ነጥብ 55 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ የተለያዩ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉም ነው ያሉት።
ለ8 ቀናት በሚቆየው የከተሞች ፎረም እንግዶች በሠላም ቆይተው በሰላም እንዲመለሱ ለሰላምና ለጸጥታ ሥራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑም ተመልክቷል።
እንግዶችን ለመቀበልም ወጣቶችን በበጎ ተግባራት በማሰማራት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መደረጉም ተገልጿል።
ሕብረተሰቡም ሰላምን በማስጠበቅና ለእንግዶቹ አስፈላጊውን ምቹ ሁኔታዎችን በማዘጋጀት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።
በማቱሣላ ማቴዎስ