Fana: At a Speed of Life!

እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የሃሳብ ኃይል ወሳኝ እንደሆነ ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የኃሳብ ኃይል ምን ያክል ወሳኝ እንደሆነ ትምህርት የሚወሰድባቸው መሆናቸውን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ መርቀው መክፈታቸው ይታወቃል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ እንደተናገሩት ፥ ኢትዮጵያ ብዙ አቅም ቢኖራትም ወደ ልማት መለወጥ ላይ ውስንነቶች አሉ።

ለዚህም በየአካባቢው ያሉ አቅሞችን በአግባቡ አይቶ፣ አቅሞችን ወደ ተጨባጭ ኃብት በመቀየር የሕዝብን ተጠቃሚነት ከማረጋግጥ አኳያ የአመራር ውስንነት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም የመሪዎች የኃሳብ አመንጪነት እንዲሁም የማስፈጸም አቅም አናሳ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመፈጠሩን ተከትሎ በሚነሱ ግጭቶች የሚመጣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ጸጋዎችን ለመጠቀም አዳጋች እንደነበርም ነው ያነሱት።

የብልጽግና ፓርቲም በሀገሪቱ በተለያዩ ሥፍራዎች ያሉ አቅሞችን አሟጦ ለመጠቀም አመራሩ ሚናውን እንዲወጣ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኃሳብ አመንጪነት ትላንት የተመረቀው የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ጎን ለጎንም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና ሀገሪቱ ያሏትን እምቅ አቅሞች እንድትጠቀም በተለይም በሀገራዊ ምክክሩ አማካኝነት ልዩነቶች እንዲፈቱ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የኃሳብ ኃይል ምን ያክል ወሳኝ እንደሆነ ትምህርት የሚወሰድባቸው መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

በተለይም የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ እንዴት መጠቀም እንደሚገባ ትልቅ ማሳያዎች መሆናቸውን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በሌላ በኩል ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲሁም በከፍተኛ የጥራት ደረጃ እንዴት ማጠናቀቅ እንደሚቻል የፕሮጀክት አመራር ጥበብን የተማርንባቸው ናቸው ሲሉም ነው የተናገሩት።

እነዚህ ፕሮጀክቶች በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰው ፥ በቀጣይም ሕዝቡን በሁሉም ደረጃ በማሳተፍ የሕዝቡን ተጠቃሚነትና የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ የተያዙ ውጥኖች እውን እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል።

በመሆኑም በቀጣይም የብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቱን አቅሞች በመጠቀም ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የጀመራቸውን ውጤታማ የአመራርነት ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.