Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው ለኢትዮጵያ የጋራ ብልጽግና መሰረት የሚጥል ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በንግግርና በምክክር ለመፍታት የጀመረችው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ለዘላቂ ሰላምና ልማት መገንባት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

ሒደቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህልን በማጎልበት ተመካካሪዎች በጋራ የተስማሙበትን ሀሳብ በመወስድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሰረት እንደሚጥል ይታመናል፡፡

ግጭቶችን እና የፖለቲካ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከሚያገለግሉ ውጤታማ ተግባራት አንዱ ምክክር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ኢትዮጵያውያን በአንድ መድረክ ተገናኝተው ስለ ሀገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ እንዲመክሩ እድል ፈጥሯል።

ይህም የዴሞክራሲ መሰረታዊ መርህ የሆነውን የመደማመጥ፣ የመቻቻልና የጋራ ውሳኔ ባሕልን ያጠናክራል።

የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ትናንት በተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ሒደቱ በአፍሪካ አህጉር የሰላም ግንባታና የዴሞክራሲ ማጠናከሪያ ጥረቶች ውስጥ እንደ መልካም ተሞክሮ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰላም፣ መረጋጋትና አንድነት ለአህጉሪቱ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ÷ የአፍሪካ ህብረት ይህንን ታሪካዊ ሒደት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

የመንግሥት ባለ ድርሻ አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የወጣቶችና ሴቶች ንቁ ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔ መሳካት ወሳኝ ነው።

ኢትዮጵያ የወደፊቷን እጣ ፈንታ በጋራ ለመወሰን የጀመረችው ይህ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ከፖለቲካ ሒደት በላይ ሀገራዊ እሴት ነው።

የሀራዊ ምክክር ጉባዔው ስኬት የአንድ ተቋም ወይም የአንድ ቡድን ስኬት ብቻ ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የጋራ ብልጽግና ጉዞ መሰረት እንደሚጥል ይታመናል፡፡

ይህንን ሒደት በመቻቻልና በጋራ ኃላፊነት ማጠናከር የሁሉም ዜጎች ድርሻ ነው፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.