በቦሌ ክፍለ ከተማ በተደረገ ክትትል 5 ፌስታል አደንዛዥ ዕፅ ተያዘ On Dec 25, 2023 528 አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በኅብረተሰቡ ጥቆማ መሠረት በተደረገ ክትትል አምስት ፌስታል አደንዛዥ ዕፅ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ በተጨማሪም በክፍለ ከተማው ወረዳ 3 በተለምዶ ወርቁ ሕንፃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተከራይቶ ይኖር የነበረ ግለሰብ ካናቢስ ከተባለው አደንዛዥ ዕፅ ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ግለሰቡ አደንዛዥ ዕፅ እያሸገ ቤቱ ውስጥ እንደሚሸጥ ለፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሠረት በተደረገ ክትትል ለሽያጭ ከተዘጋጀ አደንዛዥ ዕፅ ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡ ዕፁን ከሻሸመኔ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ እንደሚያስገባም ነው ተጠርጣሪው በሰጠው ቃል የተረጋገጠው፡፡ የምሽት ጭፈራ ቤቶችን ጨምሮ ሺሻ በሚጨስባቸውና በጫት መቃሚያ ቤቶች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፖሊስ አስታውቋል፡፡ የቤት አከራዮችም እንዲህ አይነት ችግር እንዳይከሰት በየጊዜው መከታተል እና አጠራጣሪ ነገሮች ሲመለከቱም ለጸጥታ አካላት እንዲያሳውቁ ተጠይቀዋል፡፡ 528 Share FacebookTwitterTelegramWhatsAppEmailViberPrint