የጎፋ ዞን የረጅም ጊዜ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰፊ የመልማት አቅም እና የተለያዩ የሰብል ምርቶችን የሚያስገኘው የጎፋ ዞን የረጅም ጊዜ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች በጎፋ ዞን ከማህበረሰቡ ጋር መክረዋል።
ነዋሪዎች በዞኑ ሲነሱ የነበሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያኙ በመጠየቅ ፥ የመንገድ፣ የጤና አገልግሎት፣ የመብራትና የውሃ ችግሮች ሳይፈቱ እንደቆዩ በመድረኩ አንስተዋል፡፡
የመዋቅርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችም በትኩረት እንዲሰራባቸው ነዋሪዎች ለሥራ ኃላፊዎቹ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ናቸው።
የክልሉ መንግስት በበኩሉ የቅርብና የረጅም ጊዜ እቅዶች ተቀምጠው ጥያቄዎቹ በየደረጃው ምላሽ እንዲያገኙ ስራ መጀመሩን ገልጿል።
አቶ ጥላሁን ከበደ በዚሁ ወቅት ÷ ክልሉ ፈጣን ምላሽ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ስራዎቹ ሕጋዊ አሰራርን ተከትለው እንዲፈጸሙ አደረጃጀቶችን በማጠናከር ጥያቄዎችም በዚሁ አግባብ እንዲመለሱ እየተደረገ እንደሚገኝም ነው የጠቀሱት፡፡
በተለይም የመንገድ ስራ አፋጣኝ ምላሽ የሚጠይቅ በመሆኑ በጎፋ ዞንና በክልሉ ያለውን የመንገድ ችግር ለማስተካከል የተጀመሩ ስራዎችን ለማስፈጸም በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
መንገድን ጨምሮ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች ማነቆ መሆናቸውን በማንሳት ማህበረሰቡ እራሱን የልማቱ አካል እንዲያደርግም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የጠየቁት፡፡
የክልሉ መንግስት ከጎፋ ዞን ነዋሪዎች ጋር ያደረገው የመጀመሪያው የውይይት መድረክ ሲሆን ÷ በቀጣይም የተሰሩና የዘገዩ ስራዎችን መፈተሽ የሚያስችል መድረክ እንደሚዘጋጅ ተመላክቷል።
በፍሬሕይወት ሰፊው