በትግራይ ክልል የትብብር ጥምረት ማቋቋምን አስመልክቶ ምክክር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የፍልሰት ትብብር ጥምረት ለማቋቋም በሚቻልበት ቅድመ ሁኔታ ላይ የመጀመሪያ ምክክር ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ሐዲሽ ተስፋ (ፕ/ር)÷ ክልሉ በጦርነት ማግስት ላይ የሚገኝ መሆኑን በመግለጽ በተለይም ወጣቶች ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተጋላጭ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በክልሉ ምርመራና ክርክር ከሚደረግባቸው ጉዳዮች አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት በሰው የመነገድ ወንጀሎች መሆናቸውን ጠቅሰው÷ የወንጀሎቹ አፈጻጸምም የተወሳሰበና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችም ጭምር የሚሳተፉበት ሆኗል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ የጥምረቱ መቋቋም ችግሩን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ በመግለጽ የጥምረቱን መቋቋም ክልሉ እንደሚደግፈው አረጋግጠው፤ ፍትህ ቢሮው በጥምረቱ ውስጥ የሚኖረውን የመሪነት ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፍትህ ሚኒስቴርን ጨምሮ የሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማትም የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው÷ የብሔራዊ ጥምረት ጽ/ቤቱ ለትብብር ጥምረቱ ምስረታ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ ጥምረት ጽ/ቤቱ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መድረክ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የፍልሰት ተጨባጭ ሁኔታዎችን፣ የሕግና የአደረጃጀት ማዕቀፎችን የሚያሳዩ ጽሁፎች መቅረባቸውን የፍትህ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡