በሐሰተኛ ሰነድ የይዞታ ካርታ አውጥቶ ሸጧል የተባለው ተከሳሽ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐሰተኛ ሰነድ 72 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ካርታ አውጥቶ በ5 ሚሊየን ብር ሸጧል የተባለው ተከሳሽ ተፈራ አበራ ተከስተ በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ ተደራራቢ ክሶችን አቅርቦ ነበር።
በዚህም ባቀረበው 1ኛ ክስ ላይ ተከሳሹ የሙስና ወንጀልን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 1፣ ንዑስ ቁጥር 2/ሀ እና ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ስሙን ቀይሮ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በመጠቀም በመስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 01 ስር የሚገኝ ጅምር ግንባታ ላይ የነበረ 72 ካሬ ሜትር የሆነ የሌላ ግለሰብን ይዞታ ሐሰተኛ ካርታ በማውጣት ሰናይት ሃይሌ ለተባለች ግለሰብ በ5 ሚሊየን ብር መሸጡን ጠቅሶ በክሱ ላይ አስፍሯል።
በ2ኛ ክስ ላይ ዐቃቤ ሕግ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል አዋጅ ቁጥር 780 አንቀጽ 29 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በህገወጥ መንገድ ያገኘውን ገንዘብ ምንጩን መደበቅ ወንጀል ፈጽሟል በማለትም ክስ አቅርቦበታል።
በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ በዚሁ ተከሳሽ ላይ በ3ኛ ክስ የሙስና አዋጅን በመተላለፍ በሐሰተኛ ሰነድ ካርታ የወጣለትን ይዞታ ለ3ኛ ሰው በተዘዋዋሪ ተሽጧል የሚል ክስ አቅርቦበት የነበረ ቢሆንም ይህ ክስ ከአንደኛ ክስ ጋር ተጠቃሎ እንዲቀርብ በፍርድ ቤቱ በመታዘዙ ተጠቃሎ እንዲታይ ተደርጓል።
ተከሳሹ የክስ ዝርዝር ከደረሰው በኋላ ወንጀሉን አለመፈጸሙን ገልጾ የሰጠውን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦበታል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ በተከሰሰበት ድንጋጌ እንዲከላከል በሰጠው ብይን ተከሳሹ 3 የመከላከያ ማስረጃ ያቀረበ ቢሆንም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል ባለመቻሉ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶበታል።
ከዚህም በኋላ ተከሳሹ አምስት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት አቅርቧል።
በዐቃቤ ሕግ በኩል ግን የቅጣት ማክበጃ አስተያየት አልቀረበም።
ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ ያቀረበውን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ ዛሬ በዋለው ችሎት ተከሳሹን በዕርከን 29 መሰረት በ10 አመት ጽኑ እስራትና በሁለት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ