በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት ለሸማቾችና ዩኒየኖች 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እንደሚሰራጭ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የገበያ ማረጋጋት ተግባራትን ለማከናወን በክልሉ ለሚገኙ ሸማቾች እና ዩኒየኖች 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እንደሚሰራጭ የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ብዙአለም ግዛቸው እንደገለጹት÷ የገበያ ማረጋጋት ስራን ለማከናወን የዩኒየኖችን እና ህብረት ስራ ማህበራትን የመግዛት አቅም ማጠናከር አስፈላጊ ነው፡፡
በክልሉ የሚገኙ የከተማ ልማት ክላስተር የአምስት ወራት ተቋማት አፈፃፀም እና ገበያ ልማት ቢሮ የገበያ ማረጋጋት ስራዎች ውይይት በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር እየተካሄደ ነው።
በክልል ደረጃ የሚገኙ ከ1 ሺህ 400 በላይ ነባር የግብይት ማዕከላት እየገጠማቸው ያለውን ተግዳሮት በመፍታት የገበያ ማረጋጋት ተግባር እንዲያከናውኑም አቅጣጫም ተቀምጧል።
በመድረኩ ከገበያ ማረጋጋት ስራ ጋር ተያይዞ መልካም ተሞክሮ ያላቸው ከተሞች ተሞክሯቸው የቀረበ ሲሆን÷ ቢሮዎች የራሳቸውን ህብረት ስራ ማህበራት በማቋቋም ተግባራትን በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡
በመድረኩ የክልሉ የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊና የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በእሸቱ ወ/ሚካኤል