Fana: At a Speed of Life!

አንድን ግለሰብ በማገት 1 ሚሊየን ብር የጠየቁ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን ፓዊ ወረዳ አንድን ግለሰብ በማገት አንድ ሚሊየን ብር ሲጠይቁ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

አጋቾቹ መሪጌታ ሃብተማርያም አለሙ የተባሉ ግለሰብ መኖሪያ ቤት በሕገ ወጥ መንገድ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ደንብ ልብስ ለብሰው በመሄድ ለስራ ካምፕ ትፈለጋላችሁ በሚል በማጭበርበር አግተው ከአካባቢው በባጃጅ ተሽከርካሪ መሰወራቸው ተጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ በመከላከያ ሠራዊቱ ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የተገለጸው፡፡

ከአቢሲኒያ ባንክ ባለሙያዎችና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት ብሎም ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ተጠርጣሪዎችን መያዝ እንደተቻለ ተገልጿል።

የፓዊ ወረዳ ፖሊስ ሃላፊም ድርጊቱን የፈፀሙ ግለሰቦች ላይ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይም መሰል ድርጊቶችን በመከላከል የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን ቅንጅታዊ አሰራርን በመዘርጋት በትኩረት እንደሚሰራ ተነግሯል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.