የአርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያጠናክሩ ሥራዎች በቀጣናው እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምሥራቅ አፍሪካ አርብቶ አደሮችን የጋራ ተጠቃሚነትና ትስስር የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ የሚከናወን ሀገር አቀፍ የአርብቶ አደሮች ቀን በማክበር የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አሰራሮችን ገቢራዊ አድርጋለች ተብሏል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ እንድሪያስ ጌታ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ የምስራቅ አፍሪካ አርብቶ አደሮች የጋራ ችግሮችና ተመሳሳይ እድሎች አሏቸው፡፡
ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ጋር በመተባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የአርብቶ አደሮች ቀን ቀጣናዊ መልክ እንዲኖረው ተደርጓል ብለዋል፡፡
ዘንድሮ “አርብቶ አደርነት የምስራቅ አፍሪካ ህብረ ቀለም” በሚል መሪ ሀሳብ የኢጋድ አባል ሀገራትን በማሳተፍ በአዲስ አበባ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ከጥር 17 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በሚካሄደው በዚህ መርሐ ግብር የምስራቅ አፍሪካ አርሶ/አርብቶ አደሮች ኤክስፖ፣ የፓናል ውይይት፣ ኤግዚቢሽን እና የልምድ ልውውጥ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡
አርብቶ አደርነት ድንበር የለውም ያሉት እንድሪያስ (ዶ/ር)÷ ኤክስፖው የቀጣናውን አርብቶ አደሮች ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አወንታዊ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አርብቶ አደሮች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በጋራ ለመፍታትና ለመልማት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን ማውጣት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመሆኑም የቀጣናው ሀገራት መሪዎች፣ ተመራማሪዎችና አርብቶ አደሮች ከሀገራቸው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ልምድና እውቀታቸውን የሚለዋወጡበትን እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡