ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ለምስራቁ የአማራ ክፍል ልማት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ለክልሉ በተለይም ለምስራቁ የአማራ ክፍል ልማት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ከጎርጎራ በመቀጠል የ’ገበታ’ ውጥን ሁለተኛ ፕሮጀክት የሆነውን ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት መርቀው ከፍተዋል።
አቶ አረጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ሪዞርቱ የተገነባበት አካባቢ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የታላቁ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚዬም ጀምሮ ለዓድዋ ድል ክተት የታወጀበት ወረኢሉን፣ የውጫሌ ውል የተሰናዳበት ሰማዓ ንጉስን፣ ቀጥሎ ማይጨውንና የጥቁር ሕዝቦች የድል አድራጊነት ምልክት የሆነውን ዓድዋን የሚያስተሳስር የቱሪስት ፍሰት መስመር ሆኖ የሚያገለግል ነው።
ሪዞርቱ ከተገነባበት የቅርብ ርቀት በርካታ ዕድሜ ጠገብ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህብ ያለበት አካባቢ እንደሆነ ጠቅሰው÷ በመዳረሻ ልማት ችግር ምክንያት ከቱሪስት ባይተዋር ሆኖ የቆዩትን አካባቢዎች ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል።
በምስራቅ አማራ ደሴንና ኮምቦልቻን እንዲሁም በቅርብ ርቀት የሚገኙ ሳተላይት ከተሞችን በማገናኘት ወደፊት ለሚመሰረተው ታላቁ የቀጣናው ከተማ ትልቅ አቅም ሆኖ የሚያገለግል የልማት አቅም እንደሆነም አብራርተዋል።
በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩና ለሚሰማሩ በክልሉ መዋዕለ ነዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች ምሳሌና የስበት ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
እስካሁን ከተሰሩና ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ፕሮጀክቶች በዓይነቱና በቅርጹ ለየት ያለና ለአካባቢው ግርማ ሞገስን ያላበሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ በሚያምረው የሎጎ ሐይቅ ዳርቻ እንዲጀመር ሐሳብ ያመነጩትንና የወሰኑትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ፕሮጀክቱን መርተው እንዲጠናቀቅ ላደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፕሮጀክቱን ተግተው ለተገበሩ ለባለሃብቱ በላይነህ ክንዴና በተለያዩ መንገዶች ለፕሮጀክቱ ስኬት አስተዋጽዖ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በአድማሱ አራጋው