ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በማዘጋጀት ወንጀል የተከሰሰው የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሰራተኛ በእስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን በማዘጋጀት ወንጀል የተከሰሰው የሻንቡ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሰራተኛ በ8 ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ውሳኔ አሳለፈ።
የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ የሙስና አዋጅ 881/2007 ድንጋጌን መተላለፉን ጠቅሶ ሶሬሳ አፋታ ላይ ክስ መስርቶበታል።
ተከሳሹ በጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም በሻንቡ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ የተማሪዎች ምዝገባ ኦፊሰር ሆኖ ሲሰራ በተቋሙ አመራሮች ፊርማ የተዘጋጀ የሚመስል ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችና የሙያ ማረጋገጪያ ምስክር ወረቀቶችን በ34 ግለሰቦች ስም አዘጋጅቶ የተገኘ መሆኑ በክሱ ዝርዝር ላይ ተጠቅሷል።
በዚህ መልኩ የቀረበበት ክስ ለተከሳሹ እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ ተከሳሹ ወንጀሉን አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።
ይህን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃን መርምሮ በተከሰሰበት ድንጋጌ እንዲከላከል ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሹ መከላከል ባለመቻሉ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን ከመረመረ በኋላ ተከሳሹን ጥፋተኛ በተባለበት ድንጋጌ በ8 ዓመት ከ5 ወራት ጽኑ እስራትና በ1 ሺህ ብር ገንዘብ እንዲቀጣ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ