የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዩሮ ሰብዓዊ ድጋፍ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የተለያዩ ሀገራት የሚሆን የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዩሮ ሰብዓዊ ድጋፍ አጸደቀ፡፡
በዓለም ላይ በ2024 ወደ 300 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፥ የአውሮፓ ህብረት በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጋላጭ ለሆኑ ህዝቦች ድጋፍ ያደርጋል።
በዚህም ኮሚሽኑ ዘንድሮ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዩሮ በላይ የሰብዓዊ ድጋፍ በጀት አጽድቋል።
ወደ 346 ሚሊየን ዩሮ የሚጠጋው ድጋፍ ግጭት ውስጥ ለቆዩ እና ለአየር ንብረት ለውጥ ለተጋለጡ በምስራቅ፣ ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣናዎች እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች ለሚገኙት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ማዳጋስካር፣ ሞዛምቢክ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያና ሶማሊያ የሚውል ነው፡፡
በተጨማሪም ወደ 200 ሚሊየን ዩሮ የሚጠጋው ደግሞ ለተፈናቀሉ፣ አጣዳፊ እና ሥር የሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና የተፈጥሮ አደጋዎች በተከሰተባቸው (ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ሞሪታኒያ እና ኒጀር) እንዲሁም በግጭት፣ በፀጥታ ማጣትና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገኙት የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እና የቻድ ሀይቅ ተፋሰስ (ቻድ፣ ካሜሩን እና ናይጄሪያ) የሚውል ነው፡፡
በጋዛ እና በፍልስጤም እንዲሁም በሶሪያ፣ በሊባኖስ፣ በየመን እና አጎራባች ሀገራት ያለውን ቀጣናዊ ቀውስ በተመለከተ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ወደ 470 ሚሊየን ዩሮ የሚጠጋ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚመመደብም ነው የተገለጸው።
ወደ 115 ሚሊየን ዩሮ የሚጠጋው ወደ ደቡብ ምስራቅ አውሮፓ እና የአውሮፓ አጎራባቾች ድጋፍ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡
በተጨማሪም በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ላይ እየደረሰ ባለው ቀውስ ዩክሬን እንዲሁም ምእራብ ባልካን፣ ካውካሰስ እና ሶሪያ እና ቱርክን ድጋፉ ያጠቃልላል፡፡
የ186 ሚሊየን ዩሮ የሰብዓዊ እርዳታ በደቡብ እስያ እና በፓስፊክ ተጋላጭ ለሆኑ ህዝቦች እንደሚውልም ነው የተገለጸው፡፡
ይህም በዋነኝነት በማይናማር፣ በባንግላዲሽ እና በፊሊፒንስ ኮሚሽኑ የሰብዓዊ ድጋፉን እንደሚያደርግም ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ 111 ነጥብ 6 ሚሊየን ለመካከለኛውና እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም ካሪቢያን ማለትም የተለያዩ ግጭቶች ባሉባቸው ቬንዙዌላ፣ ኮሎምቢያ፣ ሃይቲ፣ መካከለኛው አሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ኢኳዶር ድጋፉ እንደሚውልም ነው የተነገረው፡፡
በዓመቱ ውስጥ ለሚፈጠሩ ድንገተኛ አደጋዎች እና ያልተጠበቁ ሰብዓዊ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት ደግሞ ወደ 315 ሚሊየን ዩሮ ይቀመጣልም ተብሏል፡፡
ከ98 ሚሊየን ዩሮ በላይ ለፈጠራ ፕሮጀክቶች እና ፖሊሲ ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎች ላይ እንደሚውልም ነው ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ የሚያመላተው፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከፈረንጆቹ 1992 ጀምሮ ከ110 በሚበልጡ ሀገራት ሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ፥ ይህም ድጋፉ በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ በሚሊየን ለሚቆጠሩ ሰዎች በኮሚሽኑ አጋር ድርጅቶች በኩል ይደርሳል ተብሏል።