የማክሮ ኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የማክሮ ኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
በግምገማ መድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምጸሀይ ጳውሎስ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።
አቶ ተመስገን ጥሩነህ በወቅቱ እንዳሉት÷ በ2016 በጀት ዓመት ስድስት ወራት በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ የተጣለውን ግብ ማሳካት የሚያስችል የተሻለ አፈጻጸም ቢመዘገብም አሁንም የአመራሩን ቁርጠኝነትና ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል።
በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በኑሮ ውድነትና በሰላም ጉዳዮች የሚስተዋሉ ችግሮችን ማረምና ሕዝብ መካስ የሚያስችሉ ስራዎችን በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ነው ያነሱት።
ለዚህም ከተቋማት መሪዎች እስከ ታችኛው መዋቅር ፈጻሚዎች ድረስ ተቋማቸውን በሙሉ አቅም በአርያነት መምራት እና ሀገርን ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
የ2016 ግማሽ ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የመሰረተ ልማትና ማህበራዊ ዘርፍ አፈጻጸምን ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ባለፉት 6 ወራት ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ያለው አፈጻጸም ዓመታዊ ዕቅዱን ማሳካት የሚያስችል ውጤት እንደታየበት ተናግረዋል።
ለአብነትም በሰብል ምርት ረገድ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 480 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተሰበሰበ ሲሆን ዘንድሮ 496 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።
በሆልቲካልቸር፣ በእንስሳትና ዓሣ ልማት እንዲሁም በሌሎች የግብርናው ዘርፎች ውጤታማ አፈጻጸም እንደተገኘ አንስተዋል።
በመስኖ ስንዴ ረገድም በግማሽ ዓመቱ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከ2 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ነው የገለጹት።
ከዚህ ባለፈም በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፣ በገቢ አሰባሰብ ረገድም የተሻለ አፈጻጸም ስለመገኘቱ አስረድተዋል።