የጋምቤላና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሰላም ግንባታ ዙሪያ ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሰላም ግንባታ ዙሪያ ዛሬ በዲማ ከተማ ተወያይተዋል፡፡
በመድረኩ የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ኡቴንግ ኡቻን፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አለሙ እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
መድረኩ በክልሎቹ በሚገኙ አዋሳኝ ዞኖችና ወረዳዎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች በጋራ በውይይትና በምክክር በመፍታት ቀጣናውን የተረጋጋና የልማት ኮሪደር ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
በቀጣናው አልፎ አልፎ የሚስተዋለው የግድያና ዝርፊያ ችግር ጥቂት ፀረ ሰላም ሃይሎችና ሽፍቶች የሚፈጥሩት ችግር እንደሆነና ሰፊውን ሕዝብ እንደማይወክል ተጠቁሟል፡፡
ስለሆነም ችግር ፈጣሪዎችን ብቻ ተከታትሎ ህግ የማስከበር ስራ በመስራት ቀጣናውን የተረጋጋና ሰላማዊ ለማድረግ በትብብር እንደሚሰሩ የክልሎቹ አመራሮች ተናግረዋል።
በሚዋሰኑ ዞኖችና ወረዳዎች የጋራ ዕቅድ በማውጣት የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን በመቅረፍ አካባቢውን የሰላምና የልማት ቀጣና ለማድረግ እንደሚሠራም አንስተዋል፡፡
በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለውን የልማት ትስስር ለማጎልበት እና ወንድማማችነትን ለማጠናከር የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ከአኙዋ ብሔረሰብ ዞን፣ ከቤንች ሸኮ ዞንና ከምዕራብ ኦሞ ዞን የሚመለከታቸው የፀጥታ ሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የዲማ፣ የቤሩ፣ የሱሪ እና የጉራፈርዳ ወረዳዎች አመራሮች መሳተፋቸውን የወረዳው ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡