በመዲናዋ የተገነባው አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ህንጻ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ የተገነባውን አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ህንጻ በዛሬው ዕለት መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡
ባለ 15 ወለል ህንጻ የሆነው አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ 592 ህፃናትን እና 887 አዋቂዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ሁለት የሲኒማ አዳራሾች እንዳሉት ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
ባለ አራት ወለል የመኪና ማቆሚያ ያሉት ሲሆን፥ በቂ የድምፅ ማስተላለፊያ ስርዓት፣ ዘመናዊ የመብራት ስርጭት፣ የአየር መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን አካቷል ነው ያሉት።
የሲኒማ ኮምፕሌክስ ህንጻው ለቢሮዎች፣ ለስቱዲዮ፣ ለሥዕልና አርት ጋለሪ፣ ለቤተመፃሕፍት፣ ለካፍቴሪያ፣ ለሱፐርማኬት፣ ለምግብ ቤት፣ ለሱቆች፣ ለውበት ሳሎን፣ ለባንክ አገልግሎት፣ የትኬት መሸጫ ቢሮዎችና ለጉብኝት አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችንም አሟልቷል።
በተጨማሪም በቅጥር ግቢው የልጆች መጫወቻ የስፖርት ሜዳ፣ የመኪና ማቆሚያ እና አረንጓዴ ስፍራዎችን ጨምሮ ለማስታወቂያ የሚሆኑ ስክሪኖች ተገጥመውለታል፡፡
አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ለኪነጥበብ ቤተሰቦችና ለከያኒያን ተጨማሪ ብስራት ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ በዚህ ስራ ላይ ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡