Fana: At a Speed of Life!

አቶ አደም ፋራህ ከቻይና ሕዝቦች የወዳጅ ሀገራት አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የቻይና ሕዝቦች የወዳጅ ሀገራት አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ያንግ ዋንሚንግን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

አቶ አደም ፋራህ በወቅቱ እንዳሉት÷ የሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት በመንግስት ለመንግስት ደረጃም ሆነ በፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጎለብት ብልጽግና ፓርቲ አበክሮ ይሰራል።

በሁሉም መስኮች ያለው የጠበቀ ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረው የሀገራቱ መርህ ለበስ ግንኙነት ወደ ተሻለ ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሻገር ብልጽግና ፓርቲ ፍላጎት እንዳለው አንስተዋል።

ሀገራቱ በጋራ ጉዳዮች ላይ በመተባበር በዘላቂነት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማስመዝገብ እየጣሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በርካታ የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኙ ጠቅሰው÷ በመሰረተ ልማት፣ በትምህርት፣ በስልጠና እና በልምድ ልውውጥ ከቻይና ለተደረጉ ድጋፎች አመስግነዋል፡፡

በቀጣይም በፓርቲ እና በመንግስት ደረጃ ላይ ያሉ ግንኙነቶችን ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ለማሻገር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ለዚህም የከተሞች እህትማማችነት ስምምነቶች፣ የዩኒቨርሲቲዎች ትብብር፣ የባህል ልውውጥ፣ የተማሪዎች የተግባራዊ እውቀት ልውውጥ እና የወጣቶች ልማት አስፈላጊዎች በመሆናቸው ጠንካራ ሥራ ሊሰራባቸው እንደሚገባ አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ እንደሆነች ገልጸው÷ በዚህም መነሻነት የብሪክስ ሀገራትን ጥምረት እስከ መቀላቀል ያደረሰ ውጤት እንዳገኘች አንስተዋል።

በቀጣይም ከወዳጅ ሀገራት ባለሃብቶች ጋር መልማት የሚችሉና ዘርፈ ብዙ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት እድሎች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

ያንግ ዋንሚንግ በበኩላቸው÷ ብልጽግና ፓርቲ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ በከተማ ልማት እና በማህበራዊ መስኮች ያገኛቸው ድሎች በርካታ መሆናቸውን ገልፀው ለተመዘገበው ስኬት ያላቸውን አክብሮት ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ ሀገራት ጥምረት አባል የሆነችው ኢትዮጵያ ለቀጠናው እና ለመላው አፍሪካ ትልቅ መነሻ ነጥብ መሆኗን በማንሳት፤ በተለያዩ መስኮች ያሉ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማስረዳታቸውን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሕዝብ ለሕዝብ ደረጃ ግንኙነቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ቻይና ፍላጎት እንዳላት ጠቅሰው፤ ለዚህ ማስፈፀሚያ ይሆን ዘንድ ያለውን የከተሞች ለከተሞች ግንኙነት ለማዳበርና ከአዳዲስ ዘጠኝ የኢትዮጵያ ከተሞች ግንኙነት ለመመስረት ብርቱ ፍላጎቶች እንዳለ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለቻይና ስትራቴጂክ አጋር እንደሆነችና በቀጣይም በሁሉም መስኮች ትብብርን በማጠናከር የሁለቱ ሀገራት የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቻይና መንግስት በኩል በትኩረት እንደሚሰራም ቃል ገብተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.