የክልሉ ህዝብ የመልማት ፍላጎቱ በጠንካራ የመንግስት መሪነት እውን ይሆናል – አቶ ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሉ ህዝብ የመልማት፣ የማደግና የመበልፀግ ፍላጎቱ በጠንካራ የመንግስትና ፓርቲ መሪነት እውን ይሆናል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በአለታ ጩኮ ከተማ ለሚገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የክልሉ ህዝብ የመልማት፣ የማደግና የመበልፀግ ፍላጎት በጠንካራ የመንግስትና ፓርቲ መሪነት እውን መሆኑን የዛሬው ፕሮጀክት ማሳያ ነው ብለዋል።
በፓርቲው መሪነት ከተጀመሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎቻችን መካከል ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ በማድረግ የህዝባችንን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው ብለዋል።
የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ስራን ለሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
የሲዳማ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ከበደ ጋናሌ በበኩላቸው÷ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው እለት የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት ፕሮጀክት 55 ሺህ ያህል ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡