በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ122 ሚሊየን ብር በላይ የማዳበሪያ ዕዳ ማስመለስ መቻሉ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት 122 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የማዳበሪያ ዕዳ ማስመለስ መቻሉ ተገለፀ።
የክልሉ የፋይናንስ ሴክተር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በወልቂጤ ከተማ ተገምግሟል።
በግምገማ መድረኩ÷ በክልሉ በባለፉት ዘጠኝ ወራት 122 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ማስመለስ መቻሉ ተመላክቷል።
የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘይቱና ኢብራሂም÷ በየመዋቅሩ የተፈፀሙ የዕቅድ ክንውን ሪፖርቶች በቀጣይ ከችግር መውጣት የሚያስችል ዕድል መኖሩን እንደሚያመላክቱ ተናግረዋል።
የተጀመሩ ዕዳን የማስመሰል ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በርብርብ መስራት ይገባል ብለዋል።
በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ፣ የመንግስት ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አያሌው ዝና÷ በየመዋቅሩ ያሉ ጅምር ተግባራት የሚበረታቱ በመሆናቸው በቀጣይ ተግባራቱን ወደ ውጤት መቀየር እንደሚገባ አሳስበዋል።
እንዲሁም በየመዋቅሩ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥናት በመለየት በዘላቂነት መቅረፍ እንደሚገባ ገልጸው፤ በዚህ ረገድ በአንዳንድ መዋቅሮች ጅምር ስራዎች እንዳሉ መጥቀሳቸውን ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡