በሽግግር ፍትሕ የሕግ ረቂቆች ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፍትሕ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ለማስተግበር በተዘጋጁ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ሀና አርዓያ ሥላሴ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አበባ እምቢያለ ፣ የአህጉራዊው የደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፖል-ሲሞን ሀንዲ እንዲሁም የዘርፉ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች በኮንፈረሰንሱ ላይ ተገኝተዋል።
በመድረኩ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ለማስተግበር የተዘጋጁ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተመላክቷል።
ወ/ሮ ሀና በዚህ ወቅት÷ መድረኩ ለፖሊሲው ትግበራ አጋዥ ሐሳቦች የሚገኙበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አሳታፊ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ግልፅ በሆነ መንገድ መዘጋጀቱን የገለጹት ወ/ሮ አበባ÷ መድረኩ የሽግግር ፍትሕ ዓላማዎችን ለማሳካት ታሳቢ አድርጎ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
የአህጉራዊው የደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፖል-ሲሞን ሀንዲ የሽግግር ፍትሕ ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ ለዚሁ ትግበራ የወሰደችውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡