Fana: At a Speed of Life!

15 ሚሊየን ጊጋ ባይት መረጃ የማከማቸት አቅም መገንባቱ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ 15 ሚሊየን ጊጋ ባይት መረጃ ማከማቸት የሚችል አቅም መገንባቷን የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መረጃን መሰረት ያደረገ የሰው ሠራሽ ቴክኖሎጂን ማልማት፣ ማበልጸግ ብሎም የመጠቀም ሥራ እያከናወነ መሆኑን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡

አንድን ስራ በዓይነት በብዛት እና በጥራት ለመሥራት የሚያስችል ደረጃውን እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ የሰው ሠራሽ ቴክኖሎጂን በማበልጸግ ላይ እንደሚገኝ የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተስፋዬ ዘውዴ ገልጸዋል፡፡

በተለይም ለዲጂታል ኢኮኖሚ ዋና አጋር የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያለውን ክፍተት ከመሙላት ባሻገር ጠንካራ አሠራርን መፍጠር መቻሉን አንስተዋል፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም በፋይናስ ዘርፉ ላይ ሐሳቦችን መለዋወጥ እና በዘርፉ ላይ የጎላ አስተዋጽዖ ማድረግ የሚችሉ ሮቦቶች መሠራታቸው እንዲሁም በሕግ ዘርፉ የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ መተግበሪያን ማበልጽግ መቻሉን ተቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም በጤና ዘርፍ የጡት ካንሰር፣ የልብ ህመም እና የቆዳ ህመሞች ሕክምናን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች ማበልጽግ መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡

አካታች የሆነ የዲጂታል ሽግግር መገባንት አስፈላጊ በመሆኑን በመገንዘብ ኢንስቲትዩቱ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ እና ሶማሊኛ ቋንቋዎችን በቴክኖሎጂ ሥርዓት ውስጥ ማስገባት ችሏል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ የምታደርገው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ  ጉዞ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ከፍተኛ አስተዋዕጾ እያበረከተ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ዲጂታል ኢኮኖሚውም በዋናነት በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እና በበይነ-መረብ ላይ የተመሰረተ  የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያጠቃልል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሶስና ዓለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.