Fana: At a Speed of Life!

ጎንደር- የጥሯ ሙሽራ

ጎንደር አርጅታለች ደብዝዛለች ብለው ለሚያሟት መልስ የምትሰጥበት ራሷን የምትገልጥበት ወር ነው፡፡ ጥር!

የታሪክ ማህደር፣ የቀድሞ ነገስታት መቀመጫ፣ የሰሜኗ እመቤት የምትሞሸርበት ወር ስሟ ነው፡፡ ጥር ሲመጣ ጎንደርን ማንሳት ግድ ይመስላል፡፡ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ እንዲሉ … ሰዎች ብቻ ሣይሆኑ ጎንደር ትሞሸራለች… ታብባለች … እንደቀድሞው እንደነገስታቷ ካባዋን ትደርባለች፡፡

እንኳን ጎንደር ተወልደው የአጣጣሚና ፊት ሚካኤልን ታቦት አጅበው… የመንበረ ጸባኦት መድሀኒያለም ድምቀት የሆነው ወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዩሃንስን ሸኝተው ከቀሀ ኢየሱስ ወደ ባህረ ጥምቀቱ ወርደው የስጋም የመንፈስም ድህነት አግኝተው፤ በቆብ አስጥል፣ ጨዋ ሰፈር፣ አምባ ጅኔ፣ ብልኮ፣ ፒያሳ፣ አራዳ፣ እንኮዬ መስክ፣ ቅዳሜ ገበያ፣ ማራኪ፣ ልደታ፣ ሆስፒታል፣ ኮሌጅ፣ ኦቶ ፓርኮ፣ አዘዞ…ሰፈሮችን ላዳረሱ እግሮች ቀርቶ አንዴ ላዩዋት ስቦ የሚያስቀር አንዳች ኃይል አላት፡፡

ለስራ ከቀዬው እንደራቀ፣ የእናቱን እቅፍ እንደናፈቀ ጥር ሲቃረብ ጎንደር አለመክተም ስሜቱ እንዲያው ነው፡፡ ሆድ ያባባል…ውል ውል ይላል!

እንግዳ ሆነው ጎንደር ሲከትሙም ‘’ወንድም…እህት‘’ ተብለው ሲጠሩ የሀገሬው ልብ የሚያሞቅ አጠራር ነውና አቤት ወንድማለም… እመት እህታለም ብለው ይመልሱ…የእንግድነት ስሜትዎን ብን አድርጎ ያጠፋልና፡፡

‘’ዘ ካሜሎት ኦፍ አፍሪካ’’ይሏታል ዓለሜው ሲያቆላምጣት! …The legendary capital of King Arthur’s kingdom and a time or place of great happiness ሲል ይተረጎማል ካሜሎት፡፡ አንድም የንጉስ አርተር መንግስት መቀመጫ፣ ሌላም የደስታ መገኛ ስፍራ ወይንም ጊዜ እንደማለት፡፡

በጥቅሉ ጎንደር- የመናገሻ ከተማ ሲሉ ይጠሯታል፡፡

ቀድሞ ጣሊያን ጎንደርን ማዕከል ለማድረግ አስቦ በፒያሳ፣ ጨዋ ሰፈር፣ አራተኛ ፎቅና በሌሎችም የገነባቸው በቢጫ ቀለም ያሸበረቁ ሕንጻዎቿ ይመስላል ‘’የለው ሲቲ‘’ ወይንም ቢጫዋ ከተማ የምትባለው፡፡

በኢትዮጵያውያን ጥበብ የተሞላ ጦርና ጀብደኝነት ጣሊያን ቢባረርም አንዳንድ ጣሊያናውያን ግን ጎንደርን የሙጥኝ ብለው ከህዝቡ ጋር ተመሳስለው ይኖሩ እንደነበር ታሪክ ይነግራል፡፡ ይህም የህዝቡ ጀግንነት በይቅር ባይነትና ደግነት የተዋዛ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ይላሉ ታሪክ ነጋሪዎች፡፡

ጎንደር ተግደርዳሪ ነው ሲሉም ሰምተው ይሆናል፡፡ ይህ ብዙ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም ነዋሪዎች የሚሰጡት ሃሳብ ስናደምጥ ግን… ዋናው ከክብር አንጻር፣ ከባህል (ማለትም በተለምዶ መደረጉ) እና ይሉኝታ ነው፡፡

በእንግድነት ቤቱ ከሄዳችሁ እንደው አፈር ስሆን… በሞቴ ይችን ብቻ ተብለው ተገልግለው ይበላሉ … ወጥቶ በማያውቅ መመገቢያ ሰሃን ወይንም ብርጭቆ ይስተናገዳሉ፤ አልጋ ተለቅቆልዎት ለእግርዎ ውሃ ሞቆልዎት የንጉስ እንክብካቤ ይደርግልዎታል፡፡ ይህም የተለመደ ለእንግዳ ክብር የመስጠት ስርዓት ነው፡፡

የአርባ አራቱ እጣን የሚታወድባት፣ የአዛን ድምጽ የማይስተጓጎልባት፤ እንደ ጃን-ተከል ዋርካ ግርማ ሞገስ የተንሰራፋባት፤ የቅኔ፣ አቋቋም፣ ድጓ መምህር፤ ጀግንነትና ደግነትን እንደካባ የለበሰችው ጎንደር ዛሬ ከተራን እያከበረች ነው፡፡ ነገ ደግሞ ጥምቀትን፡፡

ከመላው የሀገሪቱ ክፍልና ከተለያዩ የዓለም ክፍላት ናፍቆታቸውን ሊያስታግሱ ከበረከት ሊቋደሱ ከትመዋልና እንደቀደመው እንግዶቿን እያስተናገደች ትገኛለች፡፡

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.