በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ እንዴት መሳተፍ ይቻላል?
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በአብዛኛው አክሲዮን፣ የመንግስት ቦንድ፣ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ፣ የኩባንያዎች ቦንድ እና ሌሎች ቦንዶች ወደ ማዕከላዊ ቦታ መጥተው የሚገበያዩበት መድረክ ነው፡፡
መንግስትና የግሉ ዘርፍ ለሚያከናውኗቸው ኢንቨስትመንቶች ካፒታል ለማሰባሰብ አቅም በሚፈጥረው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ መሳተፍ ስለሚቻልበት መንገድ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
ማንኛውም ሰው በአቅሙ በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ መሳተፍ የሚችል ሲሆን÷ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ትላልቅ ባለሃብቶች ድረስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድልን የሚፈጥር ነው፡፡
ከጥቃቅንና አነስተኛ አንስቶ ታዳጊ ኩባንያዎችና ግዙፍ ኩባንያዎችንም አሳታፊ ነው፡፡
ከዘርፉ ተዋንያን መካከል የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ደላላዎች የሚጠቀሱ ሲሆን÷ ተገቢውን መስፈርት አሟልተው ሲገኙ የአገናኝ አባል ፍቃድን ከካፒታል ገበያ ያገኛሉ፡፡
በዚህም ኩባንያዎችን ከአክሲዮን ገዢዎች ጋር ማገናኘት፣ ክፍያ ማጠናቀቅ ላይ የሚኖርን ችግር መፍታት (ክፍያን ማቀላጠፍ) እንዲሁም ኢንቨስተሮች ውጤታማ የሚሆኑበትን አማራጭ በማማከር ሚናቸውን ይጫወታሉ።
ደላሎቹ አክሲዮን ገዢዎች በፍላጎታቸው በሚከፍቱት የኢንቨስትመንት አካውንት ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ይይዛሉ በገንዘብ አካውንት ደግሞ ገንዘብ በማስተላለፍ የሚፈለገውን አክሲዮን፣ የመንግስት ቦንድ፣ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ እና የኩባንያዎች ቦንድ መግዛት/ መሸጥ ይቻላል፡፡
ይህ በቀጥታ በመገናኘት የሚደረግ ግብይት ሲሆን÷ ቀስ በቀስ አክሲዮን ገዢው በቀጥታ ወደ ገበያው መጥቶ የሚሳተፍበት የሞባይል መተግበሪያ የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡
ይህም አክሲዮን ገዢው ባለበት ቦታ ሞባይሉን በመጠቀም መግዛትና መሸጥ እንደሚችል ከሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ሃሳብ ኖሮት ገንዘብ የሌለው ደግሞ እየተገነቡ ባሉ ስርዓቶች መሰረት ወደ ገበያው መጥቶ መስራት የሚፈልገውን፣ የደረሰበትን ደረጃ እና የመሰሳሰሉ መጠይቆችን በማስገባት ከአካባቢው (ከጓደኛ፣ ከማህበረሰቡ፣ ከዳያስፖራ እና ከመሳሰሉት) ለስራው የሚረዳውን ገንዘብ ማሰባሰብ የሚችልበትን እድል ይፈጥራል።
ከዚህም ከፍ ሲል ጥቂት ሚሊየን ማሰባሰብ የሚፈልግ ሰው ወይም ታዳጊ ኩባንያዎች የፋይናንስ ሪፖርት፣ የኩባንያ አስተዳደር፣ የህግ ተገዢነት እና ሌሎችን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልተው ገበያው ላይ ቀርበው ፋይናንስ ማሰባሰብ ይችላሉ፡፡
በፌቨን ቢሻው