ጣልያን ለኢትዮጵያ የ585 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጅታል ሽግግርና ፈጠራ መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ እድገት እውን ማድረግ የሚያስችል ከጣልያን መንግሥት የ585 ሚሊየን ብር ድጋፍ አግኝታለች።
የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ እና የጣልያን የከፍተኛ ትምህርት እና ምርምር ሚኒስትር አና ማሪያ ተፈራርመዋል።
አሕመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የጣልያን መንግሥት ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ የኢትዮጵያን የዲጅታል አገልግሎት ለማጠናከር ያግዛል።
የድጋፍ ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካል ያላት ጠንካራ ሚና የጋራ መገለጫ መሆኑን ይጠቁማል ነው ያሉት፡፡
ድጋፉ የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ግቦችን ከማሳካት ባለፈ የሁለቱን ሀገራት ትብብር የሚያሳድግ መሆኑን አንስተዋል።
የጣልያን የከፍተኛ ትምህርት እና ምርምር ሚኒስትር በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የጣልያን አጋር በመሆኗ በጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ለኢዜአ ገልጸዋል።