በሌቦቹ ላይ የተከረቸመው የብረት መዝጊያ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ለሌብነት የተመቻቸውን በር መዝጋት ላይ ያተኮረ የልማት እቅድ ነድፎ የሀገር ልማት ጠንቅ የሆነውን ሙስና ለመዋጋት ለዓመታት ሲሰራበት ቆይቷል፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት ለሌብነት የተመቻቸ ክፍት በር ትቶ አትስረቁ በማለት የሚጨበጥ ውጤት ባለማምጣቱ ሌብነት ሀገርን ዋጋ ሲያስከፍል ቆይቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ስለ ሙስና ባደረጉት ንግግር፥ ሌብነትን መዋጋትን ወንዝን በመሻገር ጉዞ መስለው አቅርበው ነበር፡፡
በዚህም መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመሆን ከዚህ የስርቆት ወንዝ የሚያሻግር ድልድይ እንደሚገነባ ቃል ገብተው ነበር፤ ይህም ዜጎች በራስ ጥረትና በቡድን ትግል ብቻ ሳይሆን በተደላደለ ድልድይ ነጻ ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የጸረ ሙስና ድርጅት የእነ ሲንጋፖርን ተሞክሮ በማሳያነት ሲያቀርብ፤ ሲንጋፖር እንዴት አደገች ሙስናንስ በምን መንገድ አስቀረች ለሚለው ምላሽ ይሰጣል፡፡
የሲንጋፖር ጉዞ በዓመታት ጥረቱ ውጤት ያመጣበት ቀዳሚ ምክንያት ሁሉንም የለውጥ ምዕራፎች በዲጂታል መሰረተ ልማት በመምራቷና የማስፈጸምያ ህግ በማበጀቷ ነው ይላል፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ከዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የተገባውን ድልድይ ለመገንባት የሄደችበት ርቀት ሲፈተሽ እውንም የሌብነቱን በር በሌቦቹ ላይ የሚከረችም ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡
ዛሬ ላይ አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም በቀናት አልያም በሳምንታት በተበታተነ የአገልግሎት ምዕራፍ ሲሰቃይ የነበረው ማህበረሰብ፤ በጣት በሚቆጠሩ ደቂቃዎች የሚገለገልበትን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እውን ማድረግ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች ከ80 በላይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች ተከፍተው የማህበረሰቡን የአገልግሎት እርካታ በተግባር ገልጠዋል፡፡
ይህም የአገልግሎት ዘርፉን የሌብነት በር ጥርቅም አድርገው ከዘጉ ድልድዮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡
ይህ መንግሥታዊ አገልግሎትን ከሌብነት የመነጠልና ሌቦችን መግብያ ቀዳዳ የማሳጣት ጥረት ደግሞ በግሉም ዘርፍ የተከተለ ተሞክሮ እያሳየ ነው፡፡
ለዚህ ማስፈጸሚያ የሚውለውና ከጊዜም ከገንዘብም በላይ የሆነው ትልቁ ሀብት የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ገና ያልተመነዘረ ትልቁ ጸጋ ሆኖ ከፊት ተቀምጧል፡፡
እያንዳንዱ ዜጋ በአንድ ማንነት የሚታወቅባትን ሀገር እውን ማድረግ እየተቻለ ባለበት በዚህ ወቅት ጠባቧን የሌብነት በር አገኘን ስለሚሉ ሌቦች እያንዳንዷ ህገወጥ እንቅስቃሴ የፍትህ ስርዓቱን እንዳያዛባው ፋይዳ መከታ ሆኖ እየመጣ ነው፡፡
ይህ የሌብነት በርን ከመዝጋት ሌቦችን እስከማሳደድ የሚዘልቀው የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፉን ጽዱና ውጤታማ ማድረግ፤ የሌቦችን ተጠያቂነት፣ የሀገር እና ሕዝብን ሀብት እስከመጠበቅ የተዘረጋ መረብ ነው፡፡
ለዚህ ማሰሪያና ማሳረጊያ የሚሆነው ደግሞ ከወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1364/2017 ፀድቆ ተግባራዊ የተደረገው የንብረት ማስመለስ አዋጅ ነው፡፡
ሕዝብን ከሌብነት ለመታደግ የተገባውን ቃል ድልድዩን በመገንባት በተግባር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፥ ሌቦች ያከማቻሉ እንጂ አይበሏትም ያሉትን ንግግር እውን የሚያደርግ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት ነው የመደመር መንግሥት ድልድዩን በመገንባት በሌቦቹ ላይ ደግሞ የብረት መዝጊያውን የከረቸመው፡፡
አሁን የመንግሥትን አገልግሎት ከማነቆ ማውጣት ብቻ ሳይሆን፤ ሌባውንም አንቆ ማውጣት የኢትየጵያ ብልጽግና ቀጣይነት የህልውና ጉዳይ ሆኗል፡፡
በአሸናፊ ሽብሩ