የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መስተዳድር ም/ቤት ካቢኔ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ካቢኔ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የክልሉ መስተደድር ምክር ቤት ካቢኔ ከተወያየባቸው አጀንዳዎች መካከል የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመቱ የ6 ወራት የአስፈጻሚ አካላት የዕቅድ ክንውን ሪፖርት ገምግሟል።
ባለፉት 6 ወራት በክልሉ በሁሉም ዘርፎች የክልሉን ማህበረሰብ የላቀ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን በጥንካሬ በመገምገም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
በክልሉ የተከናወኑ ሰላምና ፀጥታ ስራዎች የሚበረታቱ መሆኑን የገለጸው ካቢኔው÷ በቀጣይም ከሰላም ማጠናከር ጎን ለጎን ህብረተሰቡ ያሳተፈ የልማት ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክቷል።
በበጀት ዓመቱ በስድስት ወራት የታዩ ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ በማስቀጠል የተለዩ ውስንነቶችን በቀሪ ጊዜያት የዕቅድ አካል አድርጎ መሰራት እንደሚገባ ካቢኔው አቅጣጫ አስቀምጧል።
ካቢኔው በሁለተኛው አጀንዳው ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና እውቅና ለመስጠት በቀረበው አዋጅ ላይ በስፋት ውይይት አካሂዷል።
በዚህም በየደረጃው የሚገኙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለዘላቂ ሰላም እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያላቸው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አንስቷል።
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የሚፈጠሩ ያለመግባባቶችን ስር ሳይሰዱ በአካባቢው ባህል ከመፍታት ባሻገር የህብረተሰቡን አብሮነት እና አንድነትን በማጉላት የወንጀል ተግባራትን በመቀነስ ረገድ ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ተመልክቷል።
የሚሰጡት አገልግሎትም ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ቆጣቢ በመሆኑ ያለውን ባህልና እሴት ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የባህላዊ ዳኝነት ስርዓቱ በአዋጅ መቋቋሙ የሚበረታታ መሆኑን ተወያይቶበታል።
የሚከሰቱ ግጭቶችን በመቀነስ ዘላቂና አዎንታዊ ሰላም እንዲሰፍን እንደሚያግዝም መምከሩንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
መስተዳድር ምክርቤት ካቢኔው በባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና እውቅና ለመስጠት በቀረበው አዋጅ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ለክልሉ ምክር ቤት መርቷል።