ኢትዮጵያ በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር አሥተዳደር ባለስልጣን የምስረታ መድረክ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር አሥተዳደር ባለስልጣን የምስረታ የሚኒስትሮች መድረክ ላይ እየተሳተፈች ነው፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የጅቡቲ መሠረተ-ልማት እና ኢኪዩፕመንት ሚኒስትር ሀሰን ሀሙድ፣ የደቡብ ሱዳን የመንገዶች እና ድልድዮች ሚኒስትር ሲሞን ሚጆክ እና የዑጋንዳ ትራንስፖርት አገልግሎት እና መሠረተ-ልማት ተጠባባቂ ኮሚሽነር ኔልሰን ሩዌንጋ የመክፈቻ ንግግር በማቅረብ በኮሪደር ምስረታው የጋራ አጀንዳ ላይ ምክክር አድርገዋል።
ሀገራቱን የሚያገናኙ የትራንስፖርት መስመሮችን ማስተሳሰር፤ ለቀጣናው የንግድ ግንኙነት ብሎም ለመሠረተ-ልማት ዕድገት እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማስፋፋት እንደሚያግዝ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በቅርቡ በቢሾፍቱ በተደረገው ስብሰባ የኮሪደር መመስረቻ ረቂቅ ሠነድ ላይ የተለያዩ ግብዓቶችን በመጨመር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለፊርማ ዝግጁ እንዲሆን መግባባት ላይ መደረሱ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም ዛሬ የቴክኒካል ኮሚቴን የያዘ የአራቱ ሀገራት ልዑክ በጅቡቲ የኮሪደር ምስረታ ሂደት የሚፋጠንበት ነጥቦች ላይ ምክክር አድርጓል፡፡
ውይይቱ ነገም ቀጥሎ እንደሚካሄድ መገለጹን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡