አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ለሀገራችን አዳዲስ እድሎችን የሚፈጥር ነው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዛሬው ዕለት የተመረቀው አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ለከተማችን ብሎም ለሀገራችን አዳዲስ እድሎችን የሚፈጥር ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተመረቀው አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ለገጽታ ግንባታ እና ለቱሪስት መስህብነት እንደሚውል አንስተዋል፡፡
ማዕከሉ ለከተማዋ ቱሪዝም እድገት ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡
ማዕከሉ ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶችን፣ የንግድ ውይይቶችንና ስምምነቶችን፣ ባህላዊ መድረኮችንና ልዩ ልዩ ኤግዚቢሽኖችን ለማስተናገድ እንዲሁም አዳዲስ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት የንግድና የኢኮኖሚ ስምምነቶች የሚጎለብቱበት መሆኑን ጠቅሰዋል::
ማዕከሉ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ እና ክትትል ሲያደርጉ ለነበሩ አካላትም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ባለ 5 ኮከብ ዘመናዊ ሆቴል፣ ሬስቶራንቶች፣ የስፖርት፣ የጤና፣ የመዝናኛ እና የልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫን ያከተተ ግዙፍ ማዕከል ነው ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር፣ በአንድ ጊዜ እስከ 2 ሺህ ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችል ፓርኪንግ ያለዉ ሲሆን ÷ የለሚ ፓርክ እና በቀጥታ ከአየር መንገድ ጋር የሚያገናኝ ሰፊ የመንገድ መሰረተ ልማትም ከማዕከሉ ጋር ተያይዞ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ይህም ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃ፣ ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጥር ከመሆኑ በላይ እንግዶች ሲመጡ ያለምንም እንግልት ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ስፍራ እንዲያገኙ ተደርጎ የተሰራ ነው ማዕከል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡