ሶስት የቀድሞ የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ተሽከርካሪዎችን በመስረቅ የተከሰሱ ጥፋተኛ ተባሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት ሁለት ተሽከርካሪዎችን ሰርቀዋል ተብለው ክስ የቀረበባቸው ሶስት የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ዘጠኝ ከሳሾችን ጥፋተኛ ሲል የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ፍርድ ሰጠ።
ተከሳሾቹ 1ኛ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአራዳ ክ/ከ አራት ኪሎ ፖሊስ ጣቢያ የቀድሞ የፖሊስ አባልና የወንጀል መከላከል ቡድን መሪ የነበረው ዋና ሳጅን ትግሉ ሰቦቃ፣ 2ኛ እና 3ኛ ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአዲስ ከተማ ክ/ከ ፖሊስ መምሪያ የጊቢ ጥበቃ አባላት የነበሩት ኮ/ብል ዘነበ ኩማ እና ኮ/ብል መንግስቱ እንቻሌ እንዲሁም 4ኛ አቶ ላዕከ ተስፋ፣ 5ኛ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት ውስጥ የቦሌ አራብሳ ፕሮጀክት 13 ጥበቃ የነበረው መልካሙ አያና፣ 6ኛ መላኩ ካላዩ ፣ 7ኛ ከበደ ገ/እየሱስ፣ 8ኛ ወንዶሰን ወይም ኢብራሂም ረጋሳ እና 9ኛ ሮቤል ሙሉአለም ናቸው።
ተከሳሾች የማይገባቸውን ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት ቦሌ አራብሳ ፕሮጀክት 13 ውስጥ በጥበቃነት ከሚሰራው 5ኛ ተከሳሽ ጋር በጥቅም በመመሳጠር የወንጀል ድርጊቱን መፈፃማቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።
ተከሳሾቹ በዋና እና ልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 1፡00 ሰአት አካባቢ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ቦታው ቦሌ አራብሳ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የድርጅቱ የጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርቶ በድርጅቱ የተጣለበትን ሀላፊነት ወደ ጎን በመተው ከ4ኛ ተከሳሽ ጋር በመነጋገር 1ኛ እስከ 3ኛ ያሉት ተከሳሽ የፖሊስ አባላት በዕለቱ የጥበቃ ተረኛ ሰራተኛ የሆነውን ግለሰብ ለጥያቄ ትፈለጋለህ በሚል ከጥበቃ ስራው ይዘውት መሄዳቸውን በክሱ ሰፍሯል።
የዐቃቤ ሕግ ምስክርና በዕለቱ በጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው ግለሰብ ቦታውን የሚጠብቅልኝ ሰው ደውዬ ልጥራ ሲል 2ኛ እና 5ኛ ተከሳሽ በቦታው ቀርተው እኛ እጠብቃለን አንተ ሂድ ማለታቸው በክሱ ዝርዝር ቀርቧል።
በዚህም 4ኛ ተከሳሽ የዋጋ ግምቱ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆነ ሲኖትራክ ሞተሩን ያለ ቁልፍ በማስነሳት ከቦታው ይዞ ወጥቷል፤ እንዲሁም 6ኛ ተከሳሽ በተመሳሳይ የዋጋ ግምቱ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆነ ሲኖትራክ ከቦታው ይዞ መውጣቱ ተጠቅሷል።
7ኛ ተከሳሽ ደግሞ መንገድ ላይ ጠብቆ በመቀላቀል መኪናዎቹን በሌላ ተሽከርካሪ አጅበው ወደ ኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በማቅናት ተሸከርካሪዎቹን ለ8ኛ ተከሳሽ ማስረከባቸው በክሱ ተገልጿል።
በዚህም 8ኛ ተከሳሽ ለቀሪ ለተከሳሾች የአልጋ አበል በመክፈል ለአንደኛው ተሽከርካሪ ሽያጭ በሚል 600 ሺህ ብር በአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ በኩል ወደ 7ኛ ተከሳሽ የባንክ አካውንት ገቢ ማድረጉ በክሱ ዝርዝር ላይ ቀርቧል።
በጠቅላላ የዋጋ ግምታቸው 11 ሚሊየን ብር የሆኑትን ሁለት ተሽከርካሪዎች መብት ሳይኖራቸው በህገወጥ መልኩ ወስደው በመሰወር የተሽከርካሪዎቹ ህጋዊ ባለቤት ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሱ በመሆኑ በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ተከሶሾቹ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸማቸው ክደው በመከራከራቸው ዐቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።
ዘጠኙም ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው ሲሆን የቅጣት አስተያየት ለመስማት ችሎቱ ለመጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሲፈን መኮንን