የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን ይኖራቸዋል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት በ2017/18 የክረምት ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ላይ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን ይኖራል አለ።
በኢንስትቲዩቱ የትንበያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በዘንድሮው ክረምት የደቡብ እና ምስራቅ ትግራይ፣ የሰሜን እና ደቡብ ወሎ እንዲሁም የአፋር ክልል ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እና ስርጭት ይኖራቸዋል።
ከምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተጨማሪ የመካከለኛው እና ምዕራብ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ እና ጋምቤላ ክልል ዞኖች በተመሳሳይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እና ስርጭት ይኖራቸዋል ብለዋል።
በተጨማሪም የመካከለኛው ኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፣ የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች በተመሳሳይ የዝናብ መጠን እና ስርጭት የሚያገኙ አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የክረምቱ የዝናብ ስርጭት በምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀድሞ መጀመሩን አንስተው÷ 60 በሚደርሱ የሀገራችን አካባቢዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊሜትር እስከ 70 ሚሊሜትር የደረሰ ከባድ የዝናብ መጠን ተመዝግቧል ብለዋል።
በመጪዎቹ ሐምሌ እና የነሐሴ ወራትም ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ የዝናብ መጠን እንደሚኖር ያነሱት አሳምነው (ዶ/ር÷) በተለይም ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እና ከተሞች ቅጽበታዊ ጎርፍ የመከሰት ዕድል መኖሩን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በከተሞች አካባቢ ያለውን የውሃ መፋሰሻዎች ከወዲሁ የማጽዳት ስራ መሰራት እንዳለበትና በተፋሰሶች አካባቢ አስፈላጊ የሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በግብርና ማሳዎች አካባቢ የውሃ መፋሰሻ ቦዮችን በማውጣት ሊደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ መቀነስ እና መከላከል እንደሚቻል ጠቁመው÷ ኢኒስትቲዩቱ ማንኛውንም አስጊ የአየር ሁኔታ በሚኖርበት ወቅት አስቀድሞ እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል።
በዮናስ ጌትነት