በአማራ ክልል 329 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ተከናወነ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የመንገድ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ መንገድ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ከዞን መምሪያዎች እና ባለ ድርሻ አካላት ጋር የ7 ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እያካሄደ ነው።
የቢሮው ሃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷በክልሉ የመንገድ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረትና በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
በተያዘው ዓመት 2 ሺህ 48 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ለማከናወን ታቅዶ 329 ኪሎ ሜትር መሰራቱን ጠቁመው÷ ከዚህ ውስጥም 58 ኪሎ ሜትሩ የአስፋልት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል 17 ሺህ ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ለማከናውን መታቀዱን የገለጹት ሃላፊው÷ እስካሁን ከ8 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ መጠገኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሥራዎቹ በቅንጅት በመሰራታቸው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 189 የመንገድ ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ ለማስመረቅ እቅድ መያዙንም ነው ያመላከቱት፡፡
በሙሉቀን አበበ