የመንገድ ትራፊክ አደጋ መረጃ የሚይዝ መተግበሪያ ወደ ሥራ ገባ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንገድ ትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝ ሥርዓት መተግበሪያ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መግባቱ ተገለፀ፡፡
መተግበሪያው ወደ ሥራ መግባቱን የፌዴራል ፖሊስ እና የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት በጋራ በሰጡት መግለጫ ነው ያስታወቁት።
የትራፊክ አደጋ መረጃ ማሰባሰብ ሥርዓትን ያዘምናል የተባለለት መተግበሪያው÷ በማኑዋል የነበረውን አሰራር ወደ ዲጂታል ሥርዓት እንደሚቀይርም በዚህ ወቅት ተገልጿል።
መተግበሪያው ላለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ አራት ክፍለ ከተሞች፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ በጅማ እና ባሕር ዳር ከተሞች በሙከራ ላይ መቆየቱ ተመላክቷል።
ቴክኖሎጂው እንደ ሀገር የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችን የሚመዘግብ፣ የመንገድ ደህንነት ላይ የሚሠራውን ሥራ የሚያጠናክር፣ ጊዜ ቆጣቢ፣ ተአማኒነት ያለው እና የሀገር ገፅታን የሚያሳድግ መሆኑም ተጠቁሟል።
ውጭ ኩባንያ የለማ እንደሆነ የተገለጸው መተግበሪያው÷ ደህንነቱ በፌዴራል ፖሊስ መገምገሙ ተነስቷል።
በርስቴ ፀጋዬ እና ፍቅርተ ከበደ